ወንድምህ ወዴት ነው?

እግዚአብሔር ስለወንድሞቻችን ምቾት የሚነሱንን ጥያቄዎች ይጠይቀናል፡፡ ‹‹ወንድምህ ወዴት ነው?›› ስለ ታመሙ፣ ስለታሰሩና ስለተራቡ
ወንድሞቻችን በልባችን እያንዳንዳችንን ይህን ጥያቄ ይጠይቀናል፡፡ እኛ ሰዎች ስለባለንጀሮቻችን እግዚአብሔር የሚጠይቀንን ምቾት የሚያሳጣ ጥያቄ ልክ እንደ ቃየል
ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ ‹‹አላውቅም፣ የወንድሜ ጠባቂ እኔ ነኝን?›› ብዬ እጄን ከበደል ነጻ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ ወንድሙን የገደለው ቃየል ከእግዚአብሔር ፊት
ለመሸሽ ሞከረ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙን ጊዜ ምቾት የሚነሱን ጥያቄዎች ይጠይቀናል፡፡ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ይወደው እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ስዎች ስለእኔ ምን ይላሉ? እናንተስ? ብሎ ደቀመዛሙርቱን ጠየቃቸው፡፡ ዛሬም ጌታችን ጥያቄ ይጠይቀናል፣ ‹‹ያ የራበው ወንድምህ ወዴት ነው?›› ይለናል፡፡ ‹‹እርሱማ በቁምስና የእርዳታ ብር ምሳ እየበላ ነው›› ብለን እንመልሳለን፡፡ ‹‹የታመመው ወንድምህ ወዴት ነው?›› ተብለን ስንጠየቅ ‹‹እርሱማ ሆስፒታል ገብቶ የለ እንዴ?›› ‹‹ሆስፒታል ሞልቶአል አይደል?›› ‹‹መድኃኒትስ አገኘኽለት?›› ‹‹እርሱማ አያገባኝም፣ በሌላው ሰው ሕይወት ውስጥ ምን ጣልቃ አስገባኝ? ደግሞም መድኃኒት የሚሰጠው ዘመድ አያጣም›› እያልኩኝ ራሴን ነጻ አደርጋለሁ፡፡ ‹‹የታሰረው ወንድምህ ወዴት ነው?›› ‹‹አይ እርሱን ተወው፣ እንኳን ታሰረ ይገበዋል›› ‹‹ከስንቱ ወንጀለኛ ጋር መንገድ እየተጋፋን እንኖራለን!››፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን መልሶች ግን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አትሰሙም፡፡ ጌታችን ‹‹ሕገ ወጥ ሰራተኛ ነው የምትለው፣ በዓመት ዘጠኝ ወር እየሰራ፣ ያለ ዋስትና ያለእረፍት እየሰራ፣ ያ የበዘበዝከው ወንድምህ ወዴት አለ?›› ይለናል፡፡ የወንድም ፊት ስም አለው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 የተጠቀሱትን፤- የታመሙ፣ የተራቡ፣ የተጠሙ፣ የታረዙ፣ ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉ ሕጻናት፣ በሱስ የተያዙትን፣ የታሰሩትን በስም መጥራት አለብን፡፡ ወዴት ነው ያሉት? ደግመን ደጋግመን የምንጠየቀው ጥያቄ ‹‹ወንድምህ በልብህ ውስጥ ወዴት ነው?››የሚል ነው፡፡ በልቤ ውስጥ ለነዚህ ሰዎች ቦታ አለኝ ወይ፣ ወይስ ትንሽ ሳንቲም ተመጸውቼ የሚረብሸኝን ህሊናዬን ጸጥ አሰኛለሁ? ችግርን ላለመመልከት፣ ችግርን ላለመንካት፣ ከችግር ለመሸሸግ የተድበሰበሰ ምላሽ መስጠቱን ተላምደነዋል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 የተዘረዙትን በምናውቃቸው ስሞች ተክተን ካልጠራናቸው፣ በሩ ፊት የቆመው ኃጢአት
ወደ ውስጥ ገብቶ ለማጥፋት የተዘጋጀውን የጨለማ ሕይወት በዙሪያችን እንገነባለን፡፡ እግዚአብሔር በዘፍጥረት ውስጥ አዳምን ‹‹አዳም ሆይ፣ ወዴት ነህ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ አዳም ስላፈረ ራሱን ሸሸገ፡፡ ምናልባት በዙሪያችን ያለን ይህን ጉዳይ፣ ይህን መከራ፣ ይህን ስቃይ ልብ ብለን ላንመለከት እንችል ይሆናል፡፡ ክርስቲያኖች ራሳችንን ከእውነታ መሸሸግ የለብንም፣ ይልቅስ በተከፈተ ልቦና፣ በታማኝነትና በደስታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለወንድሞቻችን ለሚጠይቀን ጥያቄ መልስ እንስጠው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *