የዶ/ር ዓቢይ ዓህመድ ጉብኝት ወደ ቫቲካን

በአባ ኃይለገብርኤል መለቁ
በኢትዮጵያ የካፑቺን ማኅበር አባል

ሰኞ ጥር 22/2011 ዓ/ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በቫቲካን ታሪካዊ ጉብኝት በማድረግ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር ተገኛኘተው በጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡ የማነኛውም አገር  መሪ ወደ ጣሊያን አገር ለጉብኝት በሚሄድበት ጊዜ ቫቲካንን የመጎበኘት ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዶ/ር ዓቢይ አህመድ በፊት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ (ራስ ተፈሪ ተብለው በሚጠሩበት ጊዜ)እ.ኤ.አ. 24 ነሐሴ 1924 ዓ/ም በቫቲካን ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛየተገናኙ ሲሆን;እንደገና በ11 ኅዳር 1970 ዓ/ም በቫቲካን ተገኝተው ከርእሰ ሊቃነ
ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛን ጎብኝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ/ም በቫቲካን ተገኝተው ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር ተገናኝተው ነበር፡፡
ቫቲካን የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት መቀመጫ ስትሆን የጦር መሣሪያ የሌለባት በርእሰ ሊቃነ
ጳጳሳት የምትተዳደር 800ያህል ነዋሪዎች ያሉባት 110 ሄክታር መሬት ይዞታ ላይ በሮም ከተማ ውስጥ የምትገኝ አንድ
ትንሽ አገር ናት፡፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቤተክርስቲያን መሪና የቫቲካን መንግሥትም መሪ ናቸው፡፡ ቫቲካን ትንሽ አገር
ብትሆንም በዓለም ዙሪያ በርካታ ድፕሎማቶች አሏት፡፡ በ114 አገሮች ኤምባሲዎች ያላት ሲሆን የ86 አገሮች ደግሞ
በቫቲካን ዲፕሎማሲያዊ ግኑኘነት አላቸው፡፡ ቫቲካን በኢትዮጵያ ልዑካንን መድባ ወዳጅነት ከመሠረተች በጣም ቆይቷል፡፡
የመጀመሪያው የቫቲካን ተወካይ በኢትዮጵያ የተሰየመው እ.ኤ.አ. መጋቢት 25/1937 ዓ/ም ነበር፡፡ በርካታ
ኤምባሲዎችን የምትከፍትበት ዋናው ምክንያት የስብከተ ወንጌል አካልና የዓለምን መሪዎች በኤምባሲዎች
አማካይነት በዓለም ዙሪያ መልካም የፖለቲካዊ አመለካከት ለመፍጠር አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው፡፡
ቫቲካን በዓለም ደረጃ ብዙ ተደማጭነት ያላት መንግሥትም የሃይማኖት ተቋምም ናት፡፡ ለዚህም ማሳያ ምልክቶች አንዱ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ባረፉ ጊዜ እ.ኤ.አ. 10 ሚያዚያ 2005 ዓ/ም በቀብራቸው
ሥነሥርዓት ላይ ለመገኘት ከመላው ዓለም 187 የአገር መሪዎችና ተወካዮች ተገኝተው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም ተገኝተው ነበር፡፡ ባለፈው ሐምሌ 2010 ዓ/ም
የኢትዮጵያና የኤርትራ ግኑኝነት ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ በተመለሰ ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ከመላው
ዓለም ለተገኙ ምእመናን የተሰማቸውን ደስታ የገለጹ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ፍራንቸስኮስ ነበሩ፡፡
ለኢትዮጵያ ከቫቲካን ጋር ወዳጅነት ማጠናከር ማለት ከዓለም ፖሊቲካ ጋርም ግኑኝነት ማጠናከር ማለት ነው፡፡
22 ጥር 2011 ዓ/ም ከርእሰ ሊቃነ ጉብኝት በፊት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በቫቲካን ግቢ
ወደሚገኘው ወደ ኢትዮጵያ ኮሌጅ (Collegio Etiopico) በመሄድ ጉብኘት ያደረጉ ሲሆን በብፁዕ ካርዲናል
ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የሚመራ ኢትዮጵያውን ጳጳሳት፤ ካህናትና ምእመናን በሽብሸቦ አቀባበል
አድርገውላቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ይሁኑ የቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር መለስ ዜናዊ
ይህንን ሥፍራ ጎብኝተው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በቫቲካን እምብርት መኖሪያ ቤት ያላት በዓለማችን ብቸኛ አገር ናት፡፡ ይህ ስፍራ
ከጥንት ጀምሮ ለኢትዮጵያ የተሰጠ የአቢሰኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ የሚል መጠሪያ ስም የነበረው ሲሆን፤ አሁን ባለው
መልክ የታነጸው በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ እ.ኤ.አ. በ1919 ሲሆን የኢትዮጵያ ኮሌጅ ከታነጸ ልክ መቶኛ
ዓመት በማክበር ላይ በመሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ጋር መገጣጠሙ የምሥረታውን መታሰቢያ ዓመት
ለመዘከር መልካም አጋጣሚ ሆኗል፡፡
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጉት የእንኳን ደህና መጡ አቀባበል መልእክት
በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ኮሌጅ ታሪክ በንግደት አማካይነት የተጀመረ መሆኑንና ከ500 ዓመት
በላይ ያስቆጠረ፤ ሥራውን ሳያቋርጥ እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ አገር መሪዎችና የሃይማኖት
መሪዎች እየመጡ ይህንን ታሪካዊ ሥፍራ እንደሚጎበኙ ገልጸዋል፡፡ ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን የሰላም ጉዞ
እንዲያስቀጥሉና ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ኢትዮጵያን አንዲጎብኙ እንዲጓብዟቸው ጠይቋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኮሌጅ
የኢትዮጵያ ታላቅነትና ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ከቅድስት መንበር ጋር ያለንን ቅርበትና ግኑኝነት መገለጫ ነው፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት ተፈጥሮ ሰዎች እንዲለያዩ በተደረገ ጊዜ እንኳን የኢትዮጵያ ኮሌጅ ኢትዮጵውያንና
ኤርትራውያን ካህናት ያለ ምንም ልዩነት በአንድነት በማስተናገድ በአርአያነት የሚጠቀስ የአንድነት መገለጫ ሥፍራ
ሆኗል፡፡ እርሶዎ ኤርትራንና ኢትዮጵያን በማቀራረብ "የአንበሳውን ድርሻ" የተወጡ ሲሆን፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ
መቀራረብ በመሳካቱ እንኳን ደስ አሎት፤ ሰላም እንዲሰፍን ላከናወኑት ትልቅ ሥራ ከልብ አመሰግናለሁ፤ አሁንም
ግኑኝነቱ በበለጠ ዳብሮ አዲስ ታሪክ ለማየት እንመኛለን ብለዋል፡፡ ሥልጣን ኃላፊነትና አገልግሎት ነው፡ ኃይል ከመጠቀም
ይልቅ ይቅርታና ፍቅር ያሸንፋል ብለው በጀመሩት ራእይ ኢትዮጵያን ወደ ልማትና እድገት ከፍታ እንደሚመሯት አምናለሁ፤

ራስን በትህትና ዝቅ በማድረግ ሌላውን ከፍ ማድረግን ማሳየትም ትልቅ ትምህርት ነው ብለዋል፡፡ ከኃይል ይልቅ
በይቅርታና በፍቅር ሰውን ማሸነፍ ይቻላል የሚለውን የርስዎን ዓይነት ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸውን ብፁዕ ወቅዱስ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን ወደ ኢትዮጵያ ቢጋብዟቸው ለአገራችን ሆነ ለአፍርካና ለአፍርካ ቀንድም ትልቅ
ጠቀሜታ አለውና ቢጋብዟቸው ደስ ይለናል በማለት፤ እርስዎንና ቤተሰብዎን እግዚአብሔር ይባርክ፤ ኢትዮጵያንና
ኤርትራን እግዚአብሔር ይባርክ በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በበኩላቸው በቫቲካን ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኮሌጅ በመጎበኘታቸው የተሰማቸውን
ኩራትና ደስታ በአድናቆት ደጋግመው ገልጸው በጸሎት እንድንበረታ አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስለ
ተጀመረው ስለ አዲስ ግኑኝነት እግዚአብሔርን በማመሰገን ወዳጅነታችን ዳብሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የንግግራቸውም ፍሬ ሀሳብ በአጭሩ እንደሚከተለው ነው፡፡ የካቶሊክ ቤተክርሰቲያን ኢትዮጵያ ታላቅ አገር መሆኗን
አሳይታለች፤ ስለዚህ ሥፍራ እስካሁን በደንብ አልተነገረልንም ነበር፤ ሕዝባችንን ይህንን ታሪክ አያውቅም፡፡ እኛ
ኢትዮጵያን ብዙ ነገር ያለን ሕዝቦች ነን፤ ነገር ግን ያለንን የማናውቅ ሕዝቦች ነን፤ትልቅነቱን የማያውቅ፤ ታሪኩን
የማያውቅ ትንሽ መሆኑ አይቀርም ብለዋል፡፡ ብፁዕ ካርዲናል ስለ ሰላም ስለ አንድነት ሲሰብኩ እንሰማለን፤ ነገር ግን
በቫቲካን ግቢ ይህንን የሚመስል ትልቅ ቦታ እንዳለ ከመቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ምን ያህል ሰው ያውቅ
ይሁን? አባቶቻቸን ብዙ ቦታ ሄደዋል፤ እኛ ግን ታሪክ ለመሥራት ይቅርና ታሪካቸውን ለማየት ጊዜ የለንም፡፡ ራሴ ግን
ትልቅ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡ ይህን የመሰለ ነገር በቫቲካን አለ ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያውያን ጥቂቶች ይሆናሉ፡፡
አገራችን ታላቅ ናት፤ ታላቅነቷን ማስቀጠል የኛ ድርሻ ነው፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስለ አንደነትና ስለ ሰላም
አንደምትሠራ ማረጋገጫው ጊዚያዊ ችግር በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ጊዜ ቤተክርስቲያኒቷ
አለመለያየቷ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ እኛ ወንድማማቾች መሆናችንን ሁሌ ማሰብ አለብን፤ አብረን ማደግ አለብን፤ አንድ
ሕዝቦች ነን፡፡ የሁለቱ ሕዝቦች አንድነት ወደ ፊት ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ይህንን የሚያጸናው እግዚአብሔር ነው፤ያ
የሚሆነው በናንተ ጸሎት ነው፡፡ከናንተ የምፈልገው ስለ ሰላም ስለ አንድነት ስለ አብሮነት በጸሎታችሁ እንዲታስቡን ነው፡፡
ይህንን ታላቅ ታሪክ አቆይታችኋል፤ ለልጆቻችን አስተምሩ አስቀጥሉ፤ ይህንን ከሠራችሁ ኃላፊነታችሁን ተወጥታችኋል
ለማለት ይቻላል፡፡ የጋራ ታሪካችንን ስላቆያችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ እኔ በጣም በጣም ኮርቻለሁ፡፡ የካቶሊካዊት
ቤተክርስቲን ስትጠራ ኢትዮጵያ ትጠራለች፤ይህ የካቶሊክ ብቻ ሳይሆን የሁላችን ታሪክ ነው፡፡ተግባራችሁ እንዲቀጥል
እየጠየቅሁ፤ "በመምጣቴ ትልቁ ደስታ ይህንን ሥፍራ ማየቴ መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ"፤ ካሉ በኋላ በክብር
መዝገብ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
የዶ/ር ዓቢይ አህመድ የቫቲካን ጉብኝት ታሪካዊ ነው፡፡ማነኛውም የአገር መሪ ሆነ ግለሰብ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር
ለመገኛኘት ይመኛል፡፡ እርሳቸው የሐዋርያ የቅዱስ ጴጥሮስ እንደራሴ ናቸው፡፡ ከርሳቸው ጋር መገኛኘት ከአንድ አገር መሪ
ከመገኛኘት ይበልጣል፤ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው መንፈሳዊ መሪም ናቸውና፡፡ ክቡር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በአገር ውስጥ ሆነ በውጨ አገሮች በተለይም በኤኮኖሚ ጠንካራ ከሆኑ አገሮች
ያደረጉት ጉብኝት ተደማጭነትን እያስገኘላቸው ነው፡፡ ክቡር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ባሁን ጊዜ በአፍሪካ ደረጃም ትልቅ
ተደማጭነት ያተረፉ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ
መገናኘታቸው ለአገርም ለራሳቸውም ትልቅ ኩራት ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ኮሌጅ ጉብኝት በኋላ አብሮአቸው ከነበሩ ከስድስት ልዑካን ጋር በመሆን ወደ ቫቲካን በመሄድ ከርእሰ ሊቃነ
ጳጳሳት ፍራንቸሲስ ጋር በመገኛኘት ስለ ኢትዮጵያና ስለ አፍሪካ ጉዳይ ተወያይተዋል፡፡ የአፍሪካ ጉዳይ ርእሰ ቃነ ጳጳሳትን
ሆነ ዓቢይ አህመድን በጣም ከሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ውይይቱ እጅግ ግልጽና ወንድማማችነት የሰፈነበት
ነበር፡፡ ከውይይቱ በኋላም ስጦታ ተለዋውጠዋል፡፡ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ አንድ ጋቢና የክርስቶስ ትንሣኤ ሥዕል ያበረከቱ
ሲሆን፤ ይህንን ሥዕል እየተመለከትኩ እጸልይነበር ብለዋል፡፡
እንዲሁም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በበኩላቸው ራሳቸው የጻፏቸውን አራት መልእክቶችና (የወንጌል ደስታEvangelii
Gaudium 24/11/2013፤ ውዳሴ ላንተ ይሁን Laudato Si24/5/2015፤በደስታም ፈንድቁGaudete et Exsultate
19/3/2018ናየቤተሰብ ደስታ (Amoris Laetitia19/3/2016)የሚሉ መልእክቶች ያበረከቱ ሲሆን
በተጨማሪእ.ኤ.አ. ጥር 1/2019 ዓ/ም ለ52ኛ ጊዜ ለዓለም አቀፍ የሰላም ቀን "መልካም ፖሊቲካ የሰላም
አገልጋይ ነው" በሚል ርእስ ያስተላለፉትን መልእክት አበርክተዋል፡፡ እነዚህ አራቱ መልእክቶች ለሰው ሁሉ
የሚያገለግሉ፤ ስለ ስብከተ ወንጌል፤ ስለ ጋራ ቤታቸን ስለሆነቸው ስለ መሬታችን፤ ስለ ቅድስናና ስለ ቤተሰብ ፍቅር
የሚናገሩ መልእክቶች ናቸው፡፡ በመጨረሻም አንድ ሜዳሊያ ያበረከቱ ሲሆን የበቆሎ ጆሮና የወይን ዘለላ በበረሃ
የሚያሳይ ሲሆን፤ ትርጓሜውም በትንቢተ ኢሳይያስ "ምድረ በዳዋን እንደ ኤደን በረሀዋንም እንደ እግዚአብሔር
ያደርጋል" (51፡3) የሚል ነበር፡፡ በኢትዮጵያና በቫቲካን መካከል ያለው ወዳጅነት አሁንም ተጠናክሮ፤ ለምልሞና
አብቦ ለማየት እንመኛለን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መንበረ ጴጥሮስ አንድነት ይባርክ፤
ይቀድስ፤ ያጽናም፡፡

አሜን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *