ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ አባቶች እና ከኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች ስለሀገራችን ሰላም የተላለፈ የሰላም መልዕክትና ጥሪ

 

“የወገኖቻችን ሞት፣ መፈናቀልና ጉዳት በአፋጣኝ በማቆም ሁሉም ወገን ቅድሚያ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰብኣዊ ክብርና ሰላም ሊተጋ ይገባል” -
የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች

የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች እና የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራችን የሚታየውን አለመረጋጋትና ውጥረት በማርገብ ሰላማችንና አንድነታችንን ለማጠናከር የሚያስችል “ሰላም ለሁላችን፤ በሁላችን!” በሚል መሪ ቃል ወደክልሎች በመሄድ የሰላም ጉዞና ምክክር ማድረግ መጀመራችን ይታወቃል፡፡ በጉዟችንም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ከክልሉ መንግስታት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተገናኝተን በወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ ችግሮችና መፍትሔዎች ተመካክረናል፡፡


በሀገራችን አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ በመከባበርና በአንድነት ለዘመናት የኖሩ ኢትዮጵያዊያን
ወገኖቻችን በመካከላቸው አለመከባበርና አለመተማመን የሚፈጥሩ ተጨባጭ ችግሮችም
እየታዩ ስለመሆኑ ተገንዝበናል፡፡ ከዚህም ባለፈ በአንዳንድ አካባቢዎች የርስ በርስ እልቂት
የሚያስከትል ግልጽ የወጣ ግጭት ይታያል፡፡
ይህ ሁኔታ በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየውን የአንድነትና የሰላም ተስፋችን ላይ ስጋት
ፈጥሮብናል፤ የወገኖቻችን ደህንነት ጉዳይ በእጅጉ የሚያስጨንቅ ሆኖብናል፡፡ በሀገራችን ሁሉም
አካባቢዎች በሚፈጠረው ግጭት በየለቱ የንፁሀን ኢትዮጵያዊንና ኢትዮጵያዊያት ደም በከንቱ
እየፈሰሰ፣ እናቶች ዛሬም እያለቀሱ፣ በርካታ ወገኖቻችንም እየተፈናቀሉ፣ ለከፋ ስቃይና እንግልት
እየተጋለጡም ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች መነሻቸው ምንም ይሁን ምን ቅድሚያ ለሀገር ሰላምና ለወገኖቻችን ደህንነት በማሰብ ችግሮች በውይይት ሊፈቱ ይገባል፡፡  ከዚህ በኋላ በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ ምንም ዓይነት ግጭትና የሚተኮስ ጥይት ሊኖር  እንደማይገባ በጽኑ በማመን እኛ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ አባቶችና የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ በመሆን ለመላው ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ
የሰላም መልዕክትና የተማጽኖ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ስለሆነም፡-

1. በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ በተለያየ ምክንያት የሚታይ አለመረጋጋትና የርስ በርስ
ግጭት በአፋጣኝ እንዲቆም፣ ከዚህ በኋላ አንድም ሰው ሊሞት እንደማይገባ፣ ከጦር መሳሪያ አፈሙዝ የሚገኝ ሰላምም እንደሌለ እና ሂደቱ ሁላችንንም የሚጎዳና
የሚያከስር ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ በሚደርስ ሞት፣ ስቃይ፣ መፈናቀልና እንግልት በማድረስ የሚፈጠር ሰላም እንደማይኖር ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ወገን ማንኛውንም ችግር በሰላምና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ እንማጸናለን፡፡

2. የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መሪዎች ኢትዮጵያን የመምራት፣ አንድነቷን የመጠበቅ እና ዜጎቿን ከድህነትና ኃላቀርነት በማላቀቅ ዘርፈ ብዙ ችግሮቿን ለመፍታት
የሚያስችል መንግስታዊ አመራር የመስጠት ታላቅ ሀገራዊ፣ ሕዝባዊና ታሪካዊ ኃላፊነት የተሸከማችሁ እንደሆናችሁ እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ የሁላችሁም የሆነችውን
ኢትዮጵያን ስታስተዳድሩና ስትመሩ በፍፁም ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ በመገዛት በመከባበር፣ በመደጋገፍና በመናበብ መሆን ይገባዋል፤ ይጠበቃልም፡፡ ይሁን እንጂ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከላችሁ ያለው ትስስር እየላላ፣ አንዳችሁ የሌላችሁ ተቃራኒ የመሆን ሁኔታ መታየት ጀምሯል፡፡ የልዩነት ሀሳብ መኖሩ በራሱ ችግር እንዳልሆነ
የምንገነዘብ ቢሆንም የሚታዩት ምልክቶችና አዝማሚያዎች ግን ጤናማ እንደልሆኑ ተገንዝበናል፡፡ ይህ የሚታየው የልዩነት ሀሳብም ወደሕዝባችን እየተጋባ፣ ለዘመናት
በአንድነት የኖረው ሕዝባችንም አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከት አድርጎታል፡፡ ሰውን በሰውነቱ ብቻ ተቀብሎና አክብሮ ይኖር የነበረው ኢትዮጵያዊ ዕሴታችን በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸረ መሆኑም በእጅጉ ያሳስበናል፡፡ ስለሆነም ሀገርና ታሪክ የጣለባችሁን ሸክም በአርቆ አስተዋይነት፣ በጥበብና በከፍተኛ ጥንቃቄ በመያዝ፣ ቅድሚያ ለሀገራችሁ አንድነትና ለወገናችሁ ደህንነት በመጨነቅ በመካከላችሁ የሚታየውን ልዩነትና ሽኩቻ ልትፈቱ እንደሚገባ በአፅንኦት እናሳስባለን፡፡ የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮችም የሀገራችን ሰላምና አንድነት እንዲጠበቅ፣ ሁሉን አቀፍ ይቅርታና ዕርቅም እንዲመጣ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡

3. የመንግስትም ይሁን የግል የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች የምታሠራጩት አንዳንድ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ይዘትና አቀራረባቸው መላ ሕዝባችንን የማይወክሉ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንንም አደጋ ላይ የሚጥሉና አሉታዊነት የተጫናቸው መሆናቸውን እየተገነዘብን ነው፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ መግለጫ የሚሠጡ አንዳንድ አመራሮች፣ የፖለቲካ ካድሬዎች እንዲሁም ምሁራንና ግለሰቦች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አባታዊ ምክራችንን እየለገስን የመንግስትም ይሁን የግል የሚዲያ ተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን በመወጣት ለሀገራችን ሰላምና ደህንነት የድርሻችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡

4. በውጪ ሀገራት የምትገኙና የሀገራችን ጉዳይ ይመለከተናል ብላችሁ የሚዲያ ተቋም ከፍታችሁ ለሕዝባችን መረጃ በመስጠት ሥራ ላይ የተሠማራችሁ እና የማኅበራዊ ትስስር ገጽን በመጠቀም መረጃ የምታሠራጩ ወገኖቻችን የምትሠሩት ዜናና ፕሮግራም በሀገራችንና ወገናችች ላይ አንዳች ጉዳት የማያደርስ ስለመሆኑ
አስቀድማችሁ ልትጠነቀቁና ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ልታስቡልን ይገባል፡፡ በሌሎች አካላት የተሳሳተ መረጃ ሲለቀቅም መረጃውንና ምንጩን በማጣራት፣ መረጃው
የተሳሳተ መሆኑን በመግለፅ ትክክለኛው መረጃ ለወገናችን እንዲደርስ ሀገራዊና ወገናዊ ኃላፊነታችሁን ልትወጡ እንደሚገባ በአፅንኦት እናሳስባለን፡፡ በተጨማሪም የጥላቻ ንግግሮችንና መልዕክቶችን በማረም አወንታዊ መልዕክት እንድታሠራጩ እንጠይቃለን፡፡ ይህን ሳታደርጉ ቀርታችሁ በወገኖቻችሁ በሚደርሠው ጉዳት፣ እንግልትና መፈናቀል የሕሊናና የታሪክ ተጠያቂ እንደምትሆኑ ልናስታውሳችሁ እንወዳለን፡፡

5. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም በምዕራብና ምስራቅ ኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሱማሌ፣ በአፋር፣ በትግራይና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ወሰን ተሻጋሪ
የትራንስፖርት አገልግሎት በመዘጋቱ፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ሁነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት መድሐኔት፣ የምግብና የፍጆታ ሸቀጦች እና ሌሎች
መገልገያዎች ቁሳቁሶች ከመሐል አገር ወደተጠቀሱት አካባቢዎች እንዳይደርስ በመደረጉና ግንኙነት በመቋረጡ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲፈጠር ከማድረጉም
በላይ በሀገራችን ሰላም፣ አንድነትና ኢኮኖሚን በእጅጉ የሚጎዳ ተግባር እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም የፌዴራልና የክልሎች መንግስታት በጋራና በትብብር  በመስራት መንገዶች በአፋጣኝ እንዲከፈቱ መንግስታዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡ መንገዶቹ በመዘጋታቸው በወላድ እናቶች፣ በጨቅላ ሕፃናት፣ በከፍተኛ የሕክምና ክትትል ያሉ ሕሙማን እና በአጠቃላይ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ሰብኣዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በእጅጉ ሊሳስበንና ሊያስጨንቀን የሚገባው በየአካባቢያችሁ ያሉ መንገዶች እንዲከፈቱ እና ከዚህ በኋላም መንገዳችሁ እንዳይዘጋ በንቃት ልትጠብቁ እንደሚገባ እናሳስባለን፡፡

6. በየደረጃው የምትገኙ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የዕድር ናየባሕላዊ አስተዳደር መሪዎች እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶች በሀገራችን አሁን
እየታየ ያለው አለመረጋጋት፣ ውጥረትና ግጭት እንዲቆምና ችግሩ በሰላም በመፍታት የየአካባቢያችሁ ሰላም እንድትጠብቅ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተራራቁትን
በማቀራረብ እና በአጠቃላይ ይቅርታና ዕርቅ እንዲመጣ የመሪነት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

7. በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ወጣ ያሉ አዝማሚያዎች እንዲስተካከሉ፣ ሁሉም ነገር በሕግና በሥርዓት መመራት ስለሚገባው የፌዴራልና የክልሎች
መንግስታት ሕጋዊ አሠራርንና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ የሕግ የበላይነት የማስጠበቅ ሕጋዊ ኃላፊነታችሁን በከፍተኛ ጥንቃቄ ልትወጡ ይገባል፡፡

8. በሀገራችን የአመራር ለውጥ ከተደረገ ወዲህ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተወጠኑትና ሀገራዊና ቀጠናዊ ፋይዳቸው የላቀ የሆነ የሰላም፣ የደህንነትና የኢኮኖሚ
ትብብርን የሚያጠናክሩ ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ እንገነዘባለን፡፡ የተጀመሩት ሥራዎች ሀገራችንን በቀጠናው ያላትን ተሠሚነትና የመሪነት ሚናዋን ከፍ የሚያደርግ ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

9. መንግስታችን በሀገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚረዳ ተቋማዊ አሠራር እንዲኖር ለማድረግ በቅድመ ዝግጅት ሥራ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ስለሆነም ይህ የተጀመረው ሰላምን በዘላቂነት የማስፈን ሥራ እንዲሳካ እና ችግሮች ሁሉ በይቅርታና ዕርቅ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁነታችንን ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

10. በመጨረሻም የሀገራችን ሰላምና የሕዝባችን ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆንና ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ እንዲወገድና
በሀገራችን የሰላም መንፈስ እንዲሠፍን እኛ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሀገራችን ሰላም ከምንግዜውም በላይ ያስጨነቀንና ያሠጋን በመሆኑ ስለሰላማችን
እየሠራን እንገኛለን፡፡ ግጭቱ ተወግዶ የታሰበው ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆንም በመላ ሀገራችን የምትገኙ አማኞች በሙሉ እንደየእምነታችሁ ለሁለት ወራት የሚዘልቅ
ጾም፣ ጸሎትና ምኅላ በማወጅ ተማጽኗችሁን ለፈጣሪያችን እንድታቀርቡ እንጠይቃለን፡፡ በውጤቱም ሰላሟ የተረጋጋና አንድነቷ የተጠበቀ ታላቅ ኢትዮጵያ
እንደምትኖረን ተስፋችን የጸና ነው፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *