ጥንታዊ ትርጉሞች

በአባ ዳንኤል አሰፋ
(ካፑቺን ፍራንቼስካውያን የምርምርና የጽሞና ማዕከል)

ወደ ቤተ መቅደስ

ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት እቤተ መቅደሱ ድረስ፣ ማለትም የእግዚአብሔር ተራራ ድረስ መቅረብ ያስፈልጋል። ይህም በልብ ንጽሕና ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ መቅደሱ በር እንዲከፈት ያስፈልጋል። እስራኤላውያን ታቦቱን ይዘው፣ ወደ ተራራ ወጥተው ወደ ቤተ መቅደስም የሚቀርቡ ከሆነ የምናጠናው መዝሙር የመጨረሻዎቹ ቁጥሮች (መዝ 23(24)7-10) ጠለቅ ያለ ምሥጢር የሚያሳዩ ይመስላሉ። ማለትም ወደ ተራራም ለመውጣት ሆነ ወደ ቤተ መቅደሱ ለመግባት ልቡን ማንጻት የሚገባው ሕዝብ እውነተኛውን የመግባት እድል የሚያገኘው ወደ መቅደሱ በሚገባው አምላክ ተመክቶ፣ አምላኩንም ተከትሎ ነው። መቅደሱም የተሠራው የአምላክ ማደርያ እንዲሆን ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል እንዲኖር መቅደስን ሥሩልኝ እንዳለው ማለት ነው (ዘጸ 25፡8)።

ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ

የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ እንደመገኘቱ መጠን፣ ወደ መቅደስ ለመግባት በቅድምያ ወደ ኢየሩሳሌም መግባት ያሰፈልጋል። ለዚህም የከተማይቱ በር እንዲከፈት ያሻል። ቴዎዶር ዘሞፕስቱኤስትያ መዝ 23(24)ቁጥር ሰባትን ከምርኮ መልስ ከሚገኘው ደስታና እልልታ ጋር ያያይዘዋል። ንጉሥ ዳዊት ሕዝቡ ከምርኮ መልስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የተከሠተውን በዚህ መዝሙር አማካኝነት፣ እንደተነበየ ይገልጻል። እንደ ቴዎድሮስ ዘሞፕስቱኤስትያ አገላለጽ በሮቹን ከፍ የሚያደርጉት ካህናትና የሕዝቡ መሪዎች ናቸው። ስለ ከተማይቱ በር ብቻ መግለጹ፣ ስለ ቤተ መቅደስም አለመናገሩ ለምን ይሆን? በዚያን ወቅት ቤተ መቅደሱ ፈርሶ ሰለነበረና ገና ስላልተሠራ ይሆን? እስከሚሠራ ገና ሰባ ዓመት መጠበቅ ነበረባቸውና።

 

ወደ መቃብር

ሰው በዚህ ምድር ላይ ሲመላለስ ወደ መኖርያ ቤቱ መግባት እንደሚያስደስተው ሁሉ ሞቶ ወደ ማረፍያ ቤቱ ሲገባ ወይም ሲቀበር ወዳጆቹንና ዘመዶቹን ያሳዝሃል። ከዚህ ጋር በተያየዘ የአውስትርያ ነገሥታት የቀብር ሥነ ሥርዓት በጣም ያስገርማል። እስቲ አንዱ ንጉሥ ሲቀበር የሚሆነውን ለአብነት እንመልከት።

የክብር ዘበኞች የንጉሡን አስከሬን ተሸክመው በአንዲት ትንሽ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ላይ ይቆማሉ። ከእነርሱ ዋናው መኰንን በወፍራም ድምጽ በሩን ከፍቱ ብሎ የጣራል። ሆኖም በሩ ዝግ ነው፤ ከውጪ ሆኖ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የቆመውን መነዂሴ ማየት አይቻልም። መነዂሴውም ከመኰንኑ በወፈረ ድምፅ “ማነው?” ሲል ይጠይቃል። በሩ እንደተዘጋ ነው። መነዂሴውም ከውስጥ በኩል ቆሞ ላለመክፈት የወሰነ ይመስላል። የክብር ዘበኛው “እኔ የአውስትርያ ንጉሠ ነገሥት፣ የሀንጋሪ ሐዋርያዊ ንጉሥ፣ የቦኤምያ የዳመስያ፣ የክሮኤስያ፣ የስላቮንያ፣ የጋሊሲያ፣ የሎዶሜርያ፣ የኢሊርያ ንጉሥ፣ የኢየሩሳሌምም ንጉሥ፣ የአውስትርያ ልዑል፣ የቶስካኖና የክራኮቭ ሊቀ መስፍን፣ የሎሬንና የሳልዝቡርግ፣ የቲር፣ የካራንቲያ፣ የካርኒዮላና የቡኮቪና … ፍራንስ ዮሴፍ ነኝ” ይላል። የማዕረግ ስሙ መብዛቱም ትንግርት ነው። መኰንኑ የስም ዓይነት ደርድሮ እንደጨሰ ከፈተኛ ፀጥታ ይሰፍናል። ካሁን ካሁን በሩ ይከፈታል ሲባልም በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው መነዂሴ በወፍራም ድምፅ “እኔ አላውቅህም” ይላል። የጦር መኰንኑ ለሁለተኛ ጊዜ እያንኳኳ “በሩን ክፈቱ” ሲል ይጠይቃል። ለመቀበርም ፍቃድ፣ ያውም ከባድ ፍቃድ፣ ያስፈልጋል ማለት ነው። መነዂሴው ግን እንደገና “ማነው” ይላል። ሆኖም በሁለተኛው ዙር የማዕረግ ስሞች እጅጉን ይቀንሳሉ። “እኔ ንጉሠ ነገሥት ፍራንስ ዮሴፍ ነኝ” ይላል የክቡር ዘበኛው። መነዂሴውም በድጋሚ “እኔ አላውቅህም” ሲል ይመልሳል። ለሦስተኛ ጊዜ መኰንኑ እያንኳኳ “በሩን ክፈቱ” ሲል ይጮኻል። አሁንም መነሴው፣ ከውስጥ በኩል፣ በልበ ሙሉነት “ማነው? ሲል” ይጠይቃል። መኰንኑ በረጅሙ ከተነፈሰ በኋላ “ሟችና ኃጢአተኛ ምስኪኑ ፍራንስ ዮሴፍ ነኝ” ይላል በድጋሚ አካባቢው ለትንሽ ጊዜ በጸጥታ ከተዋጠ በኋላ መነዂሴው “ግባ” ይላል፣ በሩም በክብር ይከፈታል። የክቡር ዘበኞቹም በዝግታ እየተራመዱ አስከሬኑን በክብር ስፍራ ላይ ያኖሩታል። ይህ አስደናቂ ባሕልና የቀብር ሥርዓት ከመዝ 23 (24) እንደተወሰደ መረዳት አይከብድም። ነገር ግን ከአንድ ጥንታዊ ቅኔ ተነሥቶ ወደ ተግባራዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ማስተዋል፣ መመሰጥና ብርሃን ይጠይቃል። ወደ ሥርዓቱ ቁም ነገርም ስንመጣ ንጉሡን በቤተክርስትያን ውስጥ በሚገኝ መቃብር ውስጥ እንዲገባ ያስቻለው ማዕረጉና የማዕረግ ስሞቹ ሳይሆን እንደማንኛውም የሰው ልጅ ውሱንና ደካማ መሆኑ ነው። እንደ ክብር ንጉሥ ወደ እግዚአብሔር ቤት መገባት አልቻለም፤ እንደ ተራ ሰው ግን ገባ። በመቃብር ፊት ሁሉም እኩል ይሆናል፤ እኩል ይፈረዳ። በአምላክም ፊት እንዲሁ።

ወደ ሲኦል

ከላይ የተመለከትነው ጥቅስ ሰው ወደ ሞት ብቻውን እንደሚሄድ በግልጽ ያሳያል። የአውስትርያው ንጉሥ ወይንም ንግሥት ሥልጣናቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ሠራዊታቸውን አስከትለው ወደ መቃብር መውረድ አይችሉም። በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የሚያጅቧቸው በሙሉ ከሟቹ ንጉሥ ወይንም ከሟቺቷ ንግሥት ይለያሉ። በለቅሶና በዝምታ ይሸኛሉ። ወደ ሞትና ወደ ሲኦል በር በዝምታ መጓዝ ግድ ይሆናል። ይህም የሰው ልጅ ሁሉ እጣ ነው። ይህ ዝምታ እጅጉን ያስፈራል። የማይታወቅ ነገር፣ የማይታወቅ ዓለም እንደሚያስፈራ ሁሉ፣ በማይታወቅ ዓለም ውስጥ ለብቻ መሆንም ይበለጡን ያስፈራል። ሞትም የሰው ልጅ ለብቻው የሚቀምሰው ነገር ስለሆነ የፍርሃት ምከንያት ይሆናል። ከሞት ወደዚህ ያለነው፣ ከሞት ወደዚያ ያለውን መገንዘብ ያቅተናል። የዚህ ምድር ሕይወት ሲያልቅ ወሰኑ፣ አጥሩ፣ በሩ፣ መሸጋገርያው ሞት ነው። ወደ ቤተ መቅደስ፣ ወደ መኖርያ ቤት መግባት ያጽናናል ያስደስታል። አብሮ መጸለይ፣  አብሮ መሆን ይቻላል። ብቸኝነት የለም። የመቃብር፣  የሞትና የሲኦል ጉዳይ ግን የተየ ነው። በክርስትና የሃይማኖት ቀኖና ውስጥ፣ “ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል ወረደ” የሚል ትመህርት አለ። ታዲያ እንድምታው ይህንን ትምህርት ከምናጠናው መዝሙር ጋር ሲያይዘው እናያለን። በቅዳሜ ስዑር ክርስቶስ ወደ ሲኦል ወርዶ የሲኦልን በር ክፈቱ ይላል። ሲኦልን የሚጠብቀውም ሰይጣን “ማነው?” ብሎ እንደሚጠይቅ ነው። ነገር ግን ሞትን ያሸነፈውን ክርስቶስን መቋቋም ስለማይችል በሩ ይከፈትና ምርኮኞች፣ የክርስቶስ መምጣት የሚጠብቁ ነፍሳት (ዕብ 11) ነጻ ይወጣሉ። በመሠረቱ፣ በዮሐንስ ራእይ ላይ፣ ክርስቶስ የሞትና የሲኦል ቁልፎች እንዳሉት ተገልጾአል (ራዕ 1፡18) እንዲሁም ክርስቶስ ምርኮን ይዞ ወደ ሰማይ እንደወጣ (ከኤፌ 4፡8) እንማራለን። ይህም እርገቱን ያመለክታል።

ምንጭ፡- ምድርና ሞላዋ ከሚል መጽሐፍ

2008 ዓ. ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *