በአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ካቶሊክ ተማሪዎች ሕብረት ለማስተባበር ኢትዮጵያዊ ተመረጠ

በአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ካቶሊክ ተማሪዎች ሕብረት (IMCS Africa) በኮት ዲቮር ዋና ከተማ በአቢጃን 12ኛውን ጉባኤ ያካሄደ ሲሆን 60ኛ የምስረታ አመቱንም አክብሯል፡፡ የጉባዔው መሪ ሀሳብ ‹‹የአፍሪካ ወጣቶች የ60 ዓመታት ተሳትፎ በሁሉአቀፍ የሰዎቸ እደገትና የወደፊት ተግባር ላይ በሚደረግ ውይይት›› ነበር፡፡ ከ22 የአፍሪካ ሀገራት የመጡ 80 የሚሆኑ ተወካዮች እና አጋሮች በጉባዔው ተገኝተዋል፡፡ በዚህ በየአራት አመት በሚደረገው ጉባዔ የሕብረቱን ማስተባበሪያ ቢሮ ለመምራት ሁለት አስተባባሪዎች ማለትም አንድ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራት ሌላኛው ደግሞ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራት ለመምረጥ ምርጫ ይካሄዳል፡፡

አሁን በተደረገው ጉባዔ 7 እጩዎች የቀረቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ፋሲካ ላቾሬ እና ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሞንጋንዚንቢ ክዌንዞንጎ ኦሬሊ ቢሮውን ለቀጣይ አራት አመታት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ ፋሲካ ላቾሬ በባህር ዳር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ካቶሊክ ተማሪዎች ማኅበር (IMCS Bahir Dar) አስተባባሪ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከጨረሰ በኋላ በባህር ዳር ደሴ ሀገረ ስብከት በሕዝብ ግንኙነት እና ሐዋርያዊ ሥራዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ውስጥ ሰርቷል፡፡ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ለሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ካቶሊክ ተማሪዎች ማኅበራት ተጠሪ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ክረምት ወራት በናይሮቢ ኬንያ በሚገኘው በሕብረቱ የአፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮ ለሁለት ወራት የሥራ ላይ ልምምድ ወስዷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በባህር ዳር በቅዱስ ቪንሰንት የንጋት ተስፋ ካቶሊክ ትምህርት ቤት እየሰራ ሲሆን በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሶፍትዌር ኤንጂኒሪንግ ሁለተኛ ዲግሪውንም እየተከታተለ ይገኛል፡፡ ፋሲካ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ካቶሊክ ተማሪዎች ማኅበር (IMCS Ethiopia) ለእጩነት የቀረበው በሕብረቱ የአፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮ የቀረበውን የእጩ ማቅረቢያ መስፈርት በሙሉ አሟልቶ ስለተገኘ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ካቶሊክ ተማሪዎች ማኅበር (IMCS Ethiopia) በምርጫው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በጣም ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ይህን የሕብረቱን የአፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮ ለመደገፍና ሕብረቱን በአፍሪካ ደረጃ ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *