የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት በወቅቱ የአገራችን ሁኔታ ላይ ያስተላለፉት መልእክት

1. እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ይህንን መልእክት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለምእመኖቻችን ሁሉ ካለብን መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ኃላፊነት በመነሣት ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ልናስተላልፍ እንወዳለን። ሁላችንም እንደምናውቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን አበረታች የሆኑ ለውጦች እየታዩ ነው። ይቅርታን፣ እርቀ-ሰላምን፣ ምሕረትን
እና ፍቅርን መሪ ቃል በማድረግ በመንግሥት የተጀመረው ሰዎችን የማቀራረብ፣ በትብብርና በምክክር ለአገራችን ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በልማት፣ በባሕል፣ በፖለቲካ፣ በሌሎችም ዘርፎች እንዲሳተፍ የማነሣሣት ሥራ በእጅጉ ሊመሰገን የሚገባው ነው። ይህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ ሊደግፈውና ሊንከባከበው፣ ፍሬም እንዲያፈራ የበኩሉን ሊያበረክት ራሱን ማብቃት ያለበት ጉዳይ ነው።
2. ነገር ግን በበቅርቡ በተለያዩ ቦታዎች በኅብረተሰባችን ላይ የደረሰው ሁከትና የሞት አደጋ እኛንም በእጅጉ አሳዝኖናል። ቀደም ሲል በሱማሌ ክልል፣ ብሎም በጉጂ ዞን፣ በሻሸመኔ፣ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ዙርያ በተለይ በቡራዩ፣ ከታ እና አሸዋ ሜዳ በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጥቃትና ዝርፍያ ምንም ዓይነት
ማብራርያ ቢሰጠው ልንቀበለው የማንችል ኢ-ሰብአዊ ወንጀል እንደሆነ በአጽንኦት ልንገልጽ እንወዳለን። አንድን የፖለቲካ ቡድን መደገፍ ሌላውን መቃወም በፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ያለ ሂደት ነው። ነገር ግን የዘር ሐረግ እየመዘዙ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረስ በፖለቲካዊ ርእዮተዓለምም ሆነ በሰብአዊነት ተቀባይነት የሌለው
አካሄድ ነው። ይሁን እንጂ በቅርቡ በአገራችን የተፈጸመው ጥቃት ግን እጅግ አሳዛኝና ከኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብና እሴት ፍጹም የወጣ ነበር። ምክንያቱም የሰው ሕይወት አልፏል፤ ሴቶችና ሕፃናት ተደፍረዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ጥቃት ደርሶባቸው ተፈናቅለዋል። የጸጥታ አካላትም የሕዝብ አመጽ ያልሆነ አቅጣጫ እንዳይዝ በቂ ዝግጅት አድርገው በሰላማዊ መንገድ መቆጣጠር ሲኖርባቸው ይህንን
ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዳልተወጡ ያመለክታል።
3. ስለሆነም እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ጥቃትና ከፍተኛ ማኅበራዊ ችግር ባጋጠመበትና ሕዝባችን በጭንቅ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሁኔታውን እያየን ዝም ልንል አይቻለንም። ከሁሉም በላይ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ቤተሰቦች ጥልቅ ሐዘናችንና ወገናዊነታችንን ስንገልጽ ሁላቸውንም በጸሎታችን እንደምናስታውቸው ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን። የሰላም ንጉሥ የሆነው የክርስቶስ ደቀመዝሙር እንደመሆናች ማንኛውንም
ጥቃት፣ ሁከትና ብጥብጥ ልንቀበል አይቻለንም እናወግዛለንም። ጥቃትና ሁከት በማናቸውም መልኩ ፍትሕና እኩልነትን ሊያመጣ አይችልም። ሁከት ሁከትን ይወልዳል እንጂ ሰላምንም ሊያመጣ አይችልም። ይልቁንም ዛሬ ኃይልና ጦር ተጠቅሞ ሥልጣን የተቆናጠጠ ነገ በተራው በኃይልና በጦር ሥልጣኑን ያስረክባል። “ሰይፍ
የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” (ማቴ 26፡52)። ሰላምና ፍትህ የሚሰፍነው በመካከር፣ በመቀባበል፣ በመከባበርና በመደጋገፍ ብቻ ነው።
4. ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው ሁሉ “ለግጭቶች አፈታትና ለሰላም ግንባታ ሂደት አስተዋጽኦ የማድረግ ጽኑ ፍላጎት አለን። የሃይማኖት አካላት የማንኛወም ኅብረተሰብ የሞራልና የኅሊና ነጸብራቅ እንደመሆናቸው መጠን፤ እኛም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የዚህ ኀሊና አንዱና የማይነጠል አካል ነን።”
5. ይህ በአዲስ አበባ ዙርያ የተፈጸመው ሥርዓት አልበኝነት እንደ ድንገተኛ ክስተት ብቻ ተደረጎ መወሰድ እንደሌለበት ነው። ከዚህ ጥቃት ጀርባ ሥር የሰደደ የሞራል ዝቀጠት እንዳለ አመላካች በመሆኑ የእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ከሁሉ በፊትና በላይ ቤተሰብ ውስጥ ልጆችን በመልካም ሥነምግባር ኮትኩቶ የማሳደግ ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን። በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነቱ የጅምላ ጥቃትና ማኅበራዊ አለመረጋጋት ጤናማ ያልሆነ የማኅበራዊና የፖለቲካ ሁኔታ ምልክት ነው።
6. ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ ጥቃቶችንበተለይም ብሔርን፣ ጎሣን እና ዘርን ተከትለው የሚደርሱ ጥቃቶችን በሕግ አግባብ እልባት እንዲያገኙ ማድረግአስፈላጊ ነው። ዜጎችም በመላው ኢትዮጵያ በወደዱትና በመረጡት አካባቢ የመኖር መለኮታዊና ሕገመንግሥታዊ መብታቸው እንዲጠበቅ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ይህንን ጥቃት ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ የፍትሕ ሥርዓቱ በሚያዝዘው መሠረት ተገቢና ውሳኔ እንዲያገኙና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ደግሞ በመንግሥትና የወገኔ ጥቃት ይገደኛል በሚሉ ሁሉ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እነዲደረግላቸው እንጠይቃለን። በእኛም በኩል እንደካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምእመኖቻችንና አጋሮቻችንን በማስተባበር የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። ማንም “እኔ የወንድሜ ጠባዊ ነኝን ?” (ዘፍ 4፡9) ሊል አይቻለውም፤ ምክንያቱም የወንደሙ ደምና ሥቃይ ወደ ፍትሕ ይጮኻልና።

7. በመጨረሻም፤ ለእርስ በርስ መተማመን፣ ለአንድነት፣ ለመቀባበል፣ ለመደጋገፍ፣ ለፍትህና ለሰላም መስፈን በእርቅና በይቅርታ መንፈስ የትናንቱን የቂምና ቁርሾ ምዕራፍ ዘግተን በጋራ ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ሁላችን እንድንተጋ በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ጥሪአችንን እናስተላልፈለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
አኸን፣ ጀርመን
መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም.

አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያንና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *