የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የተላለፈ መልዕክት

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያዊያን ልጆቻችን፣
ከሁሉ በማስቀደም የኢትዮጵያ ታላቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት በኢንጂነር

ስመኘው በቀለ ሕልፈት በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ ግጭቶች
ሕይወታቸወን ስላጡት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን የተሠማንን መሪርና ጥልቅ ሀዘናችንን በድጋሚ እንገልፃለን፡፡ ለተጎጂ ቤተሰቦች፣
ወዳጅ ዘመዶች እና ለመላው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ብርታትንና መፅናናትን፣ እንዲሁም የአካል ጉዳት የደረሠባቸው ሁሉ ፈጣን
ፈወስን እንዲያገኙ እየተመኘን በፀሎታችንም እናስባቸዋለን፡፡
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች ሁላችንም እንደምናስታውሰው በመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የተደረገውን የስልጣን ሽግግር
ተከትሎ ወደ ኃላፊነት የመጣውና በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ የሚመራው መንግስት ሥራውን በጀመረ እጅግ
አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ በርካታ ሀገራዊ ለውጦች ማሳየት ጀምሯል፡፡ በዚህም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ ከፍ
ወዳለው ሌላ ምዕራፍ በመሸጋገር ሂደት ላይ ትገኛለች፡፡ ሽግግሩም ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ የሕዝቦችን የለወጥ ፍላጎት የሚያረካ እና
የዜጎችን ሁለንተናዊ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አወንታዊ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ይህ ለወጥ እንዲመጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በተለያየ ደረጃ የለውጥ ፍላጎታቸውን በተለያየ መንገድ ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል፡፡ እኛ
የሃይማኖት ተቋማትም የሀገር አንድነት እንዲጠናከርና የሕዝባችን ሰላምና አብሮነት እንዲጠበቅ ሰላም ወዳድ የሆኑትን ሁሉ

በተደጋጋሚ ስናሳስብና ስንፀልይ መቆየታችን የሚታወስ ነው፡፡

በተለይም መንግሥት በሀገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲሠፍን ለሀገርና ለሕዝብ ጠቀሚታ ያላቸው አስፈላጊ የሆኑ
የሕግና የፖሊሲ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲተገብር፣ በሀገራችን ጥላቻና ግጭት ተወግዶ ሰላም፣ ይቅርታና ዕርቅ እንዲሠፍን
ሀገራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እንዲሠራ በአፅንኦት ስንጠይቅና ስናሳስብ ቆይተናል፡፡ በመሆኑም ዛሬ መንግሥታችን
በአጭር ጊዜ በወሰዳቸው እርምጃዎች በሀገራችን ሁሉን አቀፍ የሆነ ለውጥ መታየት ጀምሯል፡፡

በሀገራችን የታየው የሰላምና የአንድነት የለውጥ እንቅስቃሴው በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለፅ ሲሆን በተለይም ትኩረቱን በሰው
ልጆች ክብር፣ ልዕልናና ሰብኣዊነት ላይ መሆኑ፣ በዚህ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የአንድነትና
የመደመር ጥሪ በሁሉችንም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው አስችሏል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሀገራዊ አንድነታችን

እንዲጠናከር በሁሉም ክልሎች በመዞር ከህብረተሠቡ ጋር ተወያይተዋል፤ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ታስረው የነበሩ ዜጎች በይቅርታና
ክስ በማቋረጥ እንዲፈቱ ተደርጓል፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት ሠፍኖ የነበረውን ችግር በይቅርታና ዕርቅ
እንዲፈታ በማድረግ ሁለቱም ሀገራት ግንኙነታቸው በአዲስ መልክ እንዲጀምሩ ተደርጓል፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ወደ ሰሜን
አሜሪካ በመጓዝ የይቅርታ፣ የዕርቅና አንድነት ጥሪ በማድረግ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትወለደ
ኢትዮጵያዊያን ከመንግስት ጋር የነበረውን የጥላቻ ግንብ በይቅርታና ዕርቅ በማፍረስ፣ በምትኩ የአንድነት ድልድይ በሚገነባበት
ዙሪያ መለስ ውይይት በማድረግ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ ከፖሊቲካዊ ጉዳዮችም ባለፈ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ተፈጥረው የነበሩ
አለመግባባቶች በይቅርታና ዕርቅ እንዲፈቱ በማድረግ ሀገራዊ አንድነታችንንና አብሮነታችንን የሚያጠናክር ሥራ ተሠርቷል፡፡
የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያስችሉ አወንታዊ እርምጃዎች እየተተገበሩ ነው፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን የሚታየው የለውጥ
እንቅስቃሴ ተስፋ የሚሠጥና የሚበረታታ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡

በአንፃሩ ይህንን የለውጥ እንቅስቃሴ የማይፈልጉ ግለሠቦችና ቡድኖች ለውጡ እነሱ የቆሙለትን ዓላማ የሚጻረር መሆኑን
በመግለፅ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ እዚህም እዚያም ይታያል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች
ብሔርንና ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት በመቀስቀስ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ በሰዎች ላይ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ
ኪሳራና ውድመት ደርሷል፡፡ በግጭቱ ምክንያትም በርካታ ዜጎች መኖሪያቸው ለቀው በጊዜያዊ መጠለያ እንዲሠፍሩ በመገደዳቸው
በርካታ እናቶችና ሕፃናት ለከፋ ስቃይና እንግልት ተዳርገዋል፡፡
በአጠቃላይ የለውጥ ሂደቱን ወደምንፈልገው ደረጃ በማድረስ ሁላችንም ተጠቃሚ መሆን እንድንችል ከስሜታዊነት በመውጣት
ለውጡን በሚመጥን በእውቀት፣ በአስተዋይነትና በቅንነት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከምንም በላይ ፈጣሪን በመፍራት
ለፍትህና ለሰላም ልንቆም ይገባል፡፡ ስለሆነም ለሀገር ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት ሲባል ያለፈውን ሁሉ በይቅርታና በዕርቅ ዘግተን መጭውን ጊዜ ለልጆቻችን የተሻለ ማድረግ ስለሚገባ እኛ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ለመላው የሀገራችን ሕዝቦችና የሚከተለውን
መልዕክት እና የሰላም ጥሪ እናስተላልፋለን፡-

1. በሀገራችን አንዳንድ ቦታዎች አሁንም አለመግባባቶችና ግጭቶች እየተፈጠሩ የልጆቻችን ሕይወት እየተቀጠፈ ሲሆን
በርካታ ወገኖቻችን ከመኖርያ አካባቢያቸውም እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በእጅጉ የሳስበናል፡፡ ግጭቱን ከማንነት
ጋር በማያያዝና ሽፋን የሚያደርግ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ግጭቱ ሃይማኖታዊ ሽፋን እንዲያገኝ ጥረት
እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ግጭቱ እንዲፈጠሩ የሚሠራ አካል እንዳለ የሚያመላክቱ
ምልክቶችም ይታያሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለሀገራችንና ለህዝባን የማይጠቅም ብቻ ሳይሆን በሀገራችን የታየውን
ተስፋ ሰጭ የሰላም፣ የአብሮነትና የሀገራዊ አንድነት ጉዞው ላይ እክል በመፍጠር የለውጥ ሂደቱን ወደኋላ
እንዲመለስ ያደርገዋል፡፡ ስለሆም በሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች የሚያየው ግጭት በአጭር ጊዜ እንዲቆምና
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ሊፈታ የሚችል በተጠና መንገድ ምላሽ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡ ግጭቶቹን ሃይማኖታዊ
መልክ ለማስያዝ የሚደረገው ጥረት እያወገዝን እነዚህ አካላት ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እየጠየቅን ህብረተሰቡም
ሃይማኖታዊ ሽፋን ያደረጉ እንዲቅስቃሴዎችን ባለመደገፍ ሰላማቸውን እንዲጠብቁ በአፅንኦት እናሳስባለን፡፡

2. በሀገራችን እየታየ ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የተለያዩ አስተሳሰቦች መኖራቸውን ብናከብርም ለውጡን
በኃይል እርምጃ ለማስቆም ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ በዜጎች ላይ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት
እንዲደርስ የሚደረገውን አውዳሚ እንቅስቃሴ ሁሉ በአፅንኦት እናወግዛለን፡፡ በዚህ ተግባር የተሠማራችሁ ግለሰቦችና

ቡድኖች ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እንመክራለን፤ የሚመለከተው የመንግስት አካልም የሀገርን ሰላምና የዜጎችን
ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር አስፈላጊ የሆነ የሕግ ማስከበር ሥራ በመስራት መንግስታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ
እንጠይቃለን፡፡
3. በጉጂና በጌዲኦ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከመኖርያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ
ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን የሰብኣዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እያሳሰብን የሃይማኖት ተቋማት በልማት
ክንፎቻቸው በኩል ተገቢውን ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
4. የተወደዳችሁ ወጣት ልጆቻችን አሁን ላይ በሀገራችን እየታየ ያለው የለውጥ እውን እንዲሆን የእናንተ ተሳትፎና ድርሻ
ከፍተኛ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ለወጡን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንዲቻል ዛሬም የበኩላችሁን አስተዋፅኦ
እንድታደርጉ እንመክራለን፡፡ በተለይም በማኅበራዊ ትስስር ገፆች የሚለቀቁት አሳሳች መረጃዎች የእናንተን ስሜት
በማነሳሳት አንዱ ሌላውን አጥፊ ሆናችሁ እንድትሠለፉ ታቅዶ የሚሠራ መሆኑን ተረድታችሁ ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ
በአስተዋይነትና በብስለት ራሳችሁን እንድትጠብቁ እንመክራችኋለን፤

5. የተከበራችሁ የብዙሃን መገናኛ ባለቤቶችና ሠራተኞች ለሕዝብ የምታሠራጩት መረጃ በምታዘጋጁበት ጊዜ
ለህብረተሠቡ የሚኖረውን ጠቀሜታ እና ጠቃሚና ጎጅውን በአግባቡ በመለየት የሙያ ሥነ ምግባራችሁ
በሚፈቅድላችሁ መሠረት በጥንቃቄ እንድትሠሩ አደራ እንላለን፡፡
6. በአሁኑ ስዓት በመንግሥታችን እየታየ ያለው የይቅርታ፣ የዕርቅ፣ የምህረት፣ የፍቅርና የአንድነት አስተሳሰብ
በሃይማኖትም የሚደገፍና ጥልቅ የሆነ የአስተምህሮ መሠረት ያለው በመሆኑ ሁሌም የመንግስትዎ ገዥ መርህ ሆኖ
እንዲቀጥል እና የተዘረጉት የመንግስት የይቅርታ እና የምህረት እጆች ሳይታጠፉ የህግ የላይነት እንዲከበርና መንግስት
የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ አጥብቆ እንዲሠራ እናስባለን፡፡
7. በመጨረሻም በሀገራችን በተለያየ ደረጃ የሃይማኖት ተቋማትን የምታገለግሉ የሃይማኖት መሪዎችና የሃይማኖት
አስተማሪዎች በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ዘርንና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈጠሩ ግጭቶች ወደበሠ
ደረጃ እንዳይደርሱ የተለመደ መንፈሳዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *