ዮናስና የእግዚአብሔር ምሕረት

በአባ ዳንኤል አሰፋ

(ካፑቺን ፍራንቼስካውያን የምርምርና የጽሞና ማዕከል)

ዮናስና የእግዚአብሔር ምሕረት

ጥበቡ፣ ከነቢያት መጻሕፍት ውስጥ የሚያስገርምሽ የትኛው መጽሐፍ ነው?

ኅሊና፣ ከባድ ጥያቄ ነው። የትኛውን ልበልህ?

ጥበቡ፣ መቼም በብዙ የነቢያት መጻሕፍት ውስጥ ብዙ የሚያስገርሙ ነገሮች ይኖራሉ። እንዲያው ከሚያስደንቁሽ ውስጥ

አንዱን አንሥተን ብንወያይ ብዬ ነው እንጂ።

ኅሊና፣ እንግዲያውስ ስለ ትንቢተ ዮናስ ብንወያይስ?

ጥበቡ፣ ግሩም ነው። በዚህ መጻሕፍ ውስጥ ብዙ የሚያስገርሙ ነገሮችን መታዘብ ይቻላል።

ኅሊና፣ የሚያስቅ ነገርም ይገኝበታል። ይታይህ እስቲ እግዚአብሔር ወደ ምሥራቅ ሂድ ሲለው ወደ ምዕራብ መሸሽ። ከሰው መሸሽ ይቻላል። ግን የምሥራቅም ሆነ የምዕራብ ፈጣሪ ከሆነው መሸሽ ምን ይባላል? ብልጥነት ወይንስ ንዴት፣ የዋህነት ወይንስ ተስፋ መቍረጥ?

ጥበቡ፣ እኔ ደግሞ የእንሰሳቱ ጾም በጣም ያስገርመኛል። ማቅ መልበሳቸውም ያስደንቃል። አንዳንዶችንም ሊያስቅ ይችላል።

ኅሊና፣ ይህ ሁሉ አሕዛብ ከነቢዩ የበለጠ እግዚአብሔርን ሊፈሩ እንደሚችሉ ያሳያል። በታላቅ ትሕትናም ምሕረትን ሊሹ እንደሚችሉ ያመለክታል። ለመሆኑ ስንት ጊዜ “እገሌ” ወይንም “እነገሌ እግዚአብሔርን አያውቁትም” እንል የለ? ወይ ግሩም!

ጥበቡ፣ እንደ ነቢዩ ዮናስ አስተሳሰብ ከሆነ የነነዌ ሰዎች ምሕረት አያስፈልጋቸውም። ወይም አይገባቸውም።

ኅሊና፣ እዚህ ላይ እኮ መሰለኝ ዮናስ የሚሳሳተው።

ጥበቡ፣ እንዴት?

ኅሊና፣ “ይገባቸዋል፣ አይገባቸውም” የሚለው ቃል እኮ ከ“ምሕረት” ቋንቋና ከምሕረት ዓለም ጋር ምንም አይገናኝም።

ሲጀመር ምሕረት የሚሰጠው ሰው ስለተገባው አይደለም። ለሚገባን ነገርማ ቀድሞውንም ምሕረትን አንጠይቅም።

በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር የነነዌን ሰዎች ሊምራቸው አይገባም ማለት የምሕረትንም ምሥጢር ሆነ እግዚአብሔርን

አለመረዳት ነው።

ጥበቡ፣ ከገረሙኝ ነገሮች ሌላው ዮናስ ለመሸሽ ከወሰነ በኋላ፣ በመርከብ ውስጥ ተኝቶ ሳለ ያጋጠመው ነገር ነው። የዮናስን

ወይንም የእስራኤልን አምላክ የማያውቁ የመርከቡ ሰዎች ከማእበልና ከአደጋ ለመዳን ይጸልያሉ። ዮናስ ግን መጸለይ

አይፈልግም። ከሚሸሸው ፈጣሪ ጋር እንዴት ይነጋገር? መጸለይ አምላክን ማነጋገር አይደልምን? ከእግዚአብሔር ሲሸሽ

ከጸሎትም ሸሸ ማለት ነውና።

ኅሊና፣ አዎን በጣም የሚገርም ነገር ነው። መርከበኞቹ የችግሩ መንሥኤ ዮናስ መሆኑን ካወቁ በኋላ እንኳን እሱን ወደ ባሕር መጣል ይፈራሉ። ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳላቸው መረዳት ይቻላል።፡

ጥበቡ፣ ወደ ባሕር ሲጥሉትም እኮ እሱ ስለጠየቃቸው እንጂ በራሳቸው ተነሳሽነት አልነበረም።

ኅሊና፣ በአራት ምዕራፍ በተዋቀረው አጭር መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ለውጦች ሲከሰቱ እናያለን። ብዙ ነገሮች ይቀየራሉ፤ ነገር

ግን ከሁሉም በላይ ሐሳቡን መቀየር፣ ልቡን መስበር ያቃተው ዮናስ ነው።

ጥበቡ፣ ለምን ይህንን ልትይ ቻልሽ?

ኅሊና፣ ተመልከት፣ የነነዌ ሕዝብ ንስሓ ገባ። ተቀየረ። እግዚአብሔርም ለሕዝቡ ምሕረት አደረገ። የቅጣት ሐሳቡን ቀየረ።

ዮናስ ግን አልተቀየረም። ወደ ባሕር ተወርውሮ ነበር፤ ሊሞትም ይችል ነበር። ነገር ግን በእግዚአብሔር ምሕረት ዳነ።

ምሕረቱ ብታደነውም ገና ምሕረትን አልተቀበላትም። ከዚያም አልፎ እግዚአብሔር የነነዌን ሰዎች በመፈወስ፣ በድጋሚ፣

የምሕረትን ምሥጢር አሳየው። አሁንም ዮናስ አልተቀየረም።

ጥበቡ፣ ለምን ይሆን ዮናስ መቀየር ያቃተው?

ኅሊና፣ ምናልባት የነቢይ ሥራው ምን እንደሆነ አልጋባውም ይሆን? ነቢይ በእግዚአብሔር ስም ይናገራል። ግን ቁም ነገሩ የሚናገረው ቃል ጠብ ማለቱ ወይም አለማለቱ አይመስለኝም። የዮናስ ጭንቀት ያወጀው የቅጣት ቃል መፈጸሙ ወይንም አለመፈጸሙ ላይ ነው። ጥፋትን ስለተነበየ፣ ያስተላለፈው መልእክት ከሚቀየር ይልቅ እንዳለ የታላቂቱ ከተማ ሕዝብ ቢጠፋ ይሻለው ነበር።

ጥበቡ፣ ታዲያ ትንቢት መፈጸም የለበትም እንዴ!?

ኅሊና፣ እውነትህን ነው፣ ትንቢት ይፈጸማል። ነገር ግን የትንቢት መፈጸም ብቻውን ሊታይ አይገባውም።

ጥበቡ፣ ከምን ጋር ነው ሊታይ የሚገባው?

ኅሊና፣ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር መታየት ያስፈልገዋል።

ጥበቡ፣ እንዲህ ከሆነ የነቢይንና የትንቢትን ጉዳይ መመርመር ያስፈልጋል እያልሽ ነው?

ኅሊና፣ በሚገባ፤ የትንቢት ዋና ፍሬ ሐሳብ እኮ ንስሐና መጽናናት ናቸው። የትንቢት ዓላማ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር

መመለስ፣ አልያም ያዘነና የተከዘን የሰው ልጅ ማጽናናት ነው።

ጥበቡ፣ ይህንን እውነታ በትንቢተ ዮናስ ውስጥ የማናገኝ ከሆነ፣ በነቢዩ ግንዛቤ ላይ ችግር አለ ማለት እንችላለን።

ኅሊና፣ ይመስለኛል። ዮናስ እኮ የተጨነቀው ለእራሱ ስምና ዝና ነው። የተናገረው ከተፈጸመ እውነተኛ ነቢይ ነኝ ብሎ መኵራት ይችላል። የራሱን ክብር ሲፈልግ ግን የነነዌ ሰዎችን መዳን ረሳ። የእግዚአብሔርንም ምሕረት እንዲሁ ረሳ።

ጥበቡ፣ ግን የመጀመርያ ሽሽቱስ እንዴት ነው የሚታየው?

ኅሊና፣ የተያያዘ ይመስለኛል። እግዚአብሔር ዮናስን ወደ ነነዌ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ላከው። እንደ ነቢይ ለእግዚአብሔር

መልእክት ተጠራ። ነገር ግን ዮናስ ከእግዚአብሔር ለመሸሽ ሞከረ። ወደ ሌላ አቅጣጫ ተሳፈረ።

ጥበቡ፣ ከአምላኩ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ማንነትም የሸሸ አይመስልሽም? ከነቢይነት ማንነቱም ጭምር ማለቴ ነው።

ኅሊና፣ ትክክል፤ ከእግዚአብሔርና ከራሱ ሸሸቷል። ከተልእኮውም ሸሽቷል ማለት እንችላለን።

ጥበቡ፣ ሦስት ዓበይት ቁም ነገሮችን ሸሸ ማለት ነው፤ እግዚአብሔርን፣ የራስ ማንነትን፣ የራስ ዓላማን።

ኅሊና፣ እንደ ሰው መጠን ስናየው ዮናስን የምንመስልበት ብዙ አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። “እኔ ማነኝ?” የሚለው ጥያቄ ግራ አጋብቶን ልንዋዥቅ እንችላለን። እንዲሁም “ወዴት ነው የምሄደው?” የሚለውም ጥያቄ ሊያስጨንቀን ይችላል። በተጨማሪም “አመለካከቴ በምን ላይ የተመሠረተ ነው?” የሚለው ጥያቄ በጣም ሊያስቸግረኝ ይችላል።

ጥበቡ፣ ስለዚህ ዮናስ በማነነቱ ወይም በነቢይነቱ ላይ ያልተቀበለው ነገር ነበር ማለት ነው። አቅጣጫውም ላይ የተከሰተው

ነገር ግልጽ ነው። ወደ ነነዌ መሄድ አልተስማማውም። አመለካከቱም በእግዚአብሔር ቃል ላይ መመሥረት

አልቻልም። የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ዝግጁ አልነበረም።

ኅሊና፣ ይህንን ሁሉ ስናይ ዮናስ የትክክለኛ ነቢይ ምሳሌ ነው ለማለት ያስቸግር የለምን?

ጥበቡ፣ ታዲያ ለአብነት ካልጠቀመን፣ ለምን ዮናስ በነቢይነት ቀረበልን?

ኅሊና፣ ማስተማርማ ብዙ ነገር ያስተምራል። አንድም ነቢይ ምን ማድረግ እንደሌለበት ያስተምረናል። በእግዚአብሔር

የተጠራ ሰው ሊሳሳት እንደሚችል ማሳየት እራሱ ትልቅ ትምህርት ነው። አንድም ከነቢዩ ስሕተት እንድንማር፣

እራሳችንን እንድንመረምር፣ አቅጣጫችንን እንድንፈትሽ፣ ለእግዚአብሔር ቃል ቦታ እንድንሰጥ ያስተምረናል። አንድም

ከሰው አእምሮ በላይ ስለሆነው የአምላክ ፍቅር ያስተምረናል። አንድም ማንንም ሕዝብ፣ ማንንም ሰው ምሕረት

አይገባውም ማለት እንደማንችል ያሳስበናል። አንድም “አትፍረዱ” የሚለውን የጌታችንን ትእዛዝ እንድናስተውል

ያግዘናል።

ጥበቡ፣ መቼም ነቢይ እንደ መሆኑ መጠን፣ ዮናስ ስለ እግዚአብሔረ ምሕረት አያውቅም ማለት አንችልም።

ኅሊና፣ እሱ እኮ ነው የሚያስገርመው። እኔ እንደምረዳው ዮናስ ከእግዚአብሔር ምሕረት ጋር ጸብ ያለው ይመስላል።

ጥበቡ፣ እንዴት?

ኅሊና፣ እንደ ዮናስ ሐሳብ እግዚአብሔር አብዝቶታል። እንዴት ታላቅ ጠላት የሆነውን የነነዌን ሕዝብ ሊምር ይፈልጋል?

ጥበቡ፣ በሌላ አነጋገር ዮናስ እግዚአብሔርን ሊያርመው እየፈለገ ነው ማለት ነው። የአምላክ ምሕረት ያስቆጣውም ለዚሁ ነበር።

ኅሊና፣ የታሪኩ መጨረሻ ግን ውብ ነው። የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ፍቅርንና ቸርነትን የሚያንጸባርቅ ድንቅ ጥያቄ፦ “እኔስ

ታዲያ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ

አላስብምን?” የቃሉ ውብት ከአእምሮአችን በላይ ነው። ምሕረቱም ከእኛ አድማስ እጅጉን ይሰፋል፤ ይልቃል። በቃሉ ውበት መመሰጥ እግዚአብሔርን፣ እራስንና ተልእኮን ማግኘት ማለት ነው። እግዚአብሔርን ያገኘ እራሱን ያገኛል። እራሱን ያገኘ ደግሞ ተልእኮውን ይገነዘባል።

ምንጭ፡ ፍቅርና ሰላም ወርሃዊጋዜጣ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *