ለምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተደረገ

ለምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተደረገ

ከሐምሌ 6-16 ቀን 2010 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ለሚደረገው 19ኛው የምሥራቅ አፍሪካ  ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሕብረት የተለያየ ዝግጅት በመደረግ  ላይ ይገኛል።

ከዝግጅቱ አንዱ አካል የሆነው ታህሳስ 14 ቀን 2010 ዓ. ም. በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል የተካሄደው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት አንዱ ነበር።

የገንዘብ ማሰባሰቢው ጥሪ በዋናነት ለኢትዮጵያውን ባለሀብቶች  የቀረበ  ሲሆን የቤተክርስቲያኒቷ ጥሪ በማክበር መልስ የተገኘበት ዝግጀት ነበር።

በዚህ ምሽት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተገኙ ሲሆን ብፁዕ ካርዲናልና ብፁዐን ጳጳሳት አቀባበል አድርገውላቸዋል። በሥነሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪካ  ጳጳሳት ጉባኤዎች ሕብረት ባንዲራ በክብር ከተቀመጠ በኋላ ብፁዕ ካርዲናል  ዝግጀቱን በፀሎት ከፍተዋል። ብፁዕነታቸው ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት እና   ክብራን እንግዶችን ጥሪያችንን አክብራችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ምስጋና አቅርበዋል። የምሥራቅ አፍሪካ  ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሕብረት ከእኔ በፊትም ሆነ ኋላ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲደረግ ጥሪ ቢቀርብም በተለያየ ምክንያት እንዲያልፈን አድርገን ነበር። እ.ኤ.አ 2014 በማላዊ በተደረገው የሕብረቱ ጉባኤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ደረጃ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለማዘጋጀት ብቁ በመሆንዋ ሕብረቱ ስላመነ  ቀጣዩን ስብሰባ እንድናስተናግድ ጉባኤው  በሙሉ ድምጽ በመወሰኑ እኛም የኢትዮጵያ ሕዝብንና መንግስትን በመተማመን ጥሪውን መቀበላቸዋን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል። ህብረቱ 9 አገራትን የጳጳሳት ጉባኤዎችን እንዳቀፈ ገልፀው የመንግስትና የሕዝብ  ትብብርና ለዝግጀቱ ወሳኝ መሆኑንም አሳስበዋል። አገራችንን ታላቅነቷንና እንግዳ ተቀባይነታችን የምናሳይበት ዕድል እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ ዝግጀት የተገኙትን ሁሉ በድጋሚ በማመስገን አባታዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

በመቀጠልም ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ለቤተክርስቲያኒቷ ያላቸውን አክብሮት በመግለጽ ኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰችበትን የልማት ዕድገት በመግለጽ ለአፍሪካ ዕድገት የበኩሏን ድርሻ እንደምታበረክ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲን  የምታዘጋጀውን 19ኛ የምሥራቅ አፍሪካ  ጳጳሳት ጉባኤዎች ሕብረት መሳካት መልካሙን ሁሉ በመመኘት የመንግሥት ድጋፍ እንደማይለይ ገልጸዋል።

በዚሁ ጊዜ 19ኛው የምሥራቅ አፍሪካ  ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አርማ በተመለከተ በምስል የተደገፈ ገለጻ የተደረገ ሲሆን ክቡር አባ ሐጎስ ሐይሽ ስለ ምሥራቅ አፍሪካ  ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤዎች  ሕብረት /አሜሲያ/ ከምስረታው ጀምሮ አሁን ያለበት የዕድገት ደረጃ ገለጻ አድርገዋል። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲን  ይህን ጉባኤ ስትቀበል ዋናው መተማመኛዋ ሕዝብና መንግስት መሆኑን በመግለጽ ልግሰና ከራስ መጀመሩ ታላቅ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአደራ የተሰጣትን ሀብት ለሚመለከተው ክፍል ትሰጣለች እንጂ ሰዎች እንደሚያስቡት የራስዋ ሀብት እንደሌላትም አያይዘው ገልጸዋል። በመጨረሻም ይህ ዝግጀት በዋናነት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ አስተባባሪነት ቢካሄድም  ከጉባኤው የሚገኘው ፍሬ ለመላው  የምሥራቅ አፍሪካ  ሕዝቦች   አንድነትና ሰላም  መሰረት እንደሆነ ክቡርነታቸው ገልጸዋል።

በዚሁ ምሽት ክቡር አባ ዳንኤል አሰፋ የቅዱስ ፍራንቼስኮስ የጥናትና የምርምር ማዕከል ዲሬክተር በ19ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ መሪ ቃል “በእግዚአበሔር የተመሠረተ ሕያው ብዝሃነት ሰብዓዊ ክብር ሰላማዊ አንድነት ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ቃለ ምዕዳን በቃሉ ውበት ዓምድ ላይ ይዘን ቀርበናል።

በዚሁ ዝግጅት ዝማሪዎች  ፣የገንዘብ ልግስና ጨረታ ጊዜያቸውን ጠብቀው ተካሄደዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት፣ የተለያ ሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዝግጅቱ በብፁዕ ካርዲናል ፀሎተ ቡራኬ ተዘግቷል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *