2010 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትጵያያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የ2010 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን ” (ገላ 4፡4)

ብፁዓን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና፤ ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

በቅርብም በሩቅም  ያላችሁ ካቶሊካውያን ምዕመናንና ምዕመናት፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፣ በተለያየ የህመም ደዌ ተይዛችሁ በየቤቱና በየሐኪም ቤቶች የምትገኙ ህሙማን፣ የአገር ድንበር ለማስከበር በየአገሩና በየጠረፉ እንዲሁም ሰላም ለማስከበር በውጭ አገራት የተሰማራችሁ ኢትጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በየማረሚያ ቤቱ ያላችሁ የህግ ታራሚዎች፤ በስደት ሕይወት የምትገኙ ወገኖችና  የተወደዳችሁ ምዕመናን በሙሉ !

ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ 2010 ዓ.ም.  የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን  በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም አቀርብላቸኃለሁ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም ተወለደ፡፡ በምድርና በሰማይም ታላቅ ደስታ ሆነ ፡፡ የጥል ግርግዳ ፈርሶም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሰላምና ፍቅር ሆነ፡፡ ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔር ተገዢ መሆኑንና በሰው ዘንድ የተናቀ የሚመስለው በፈጣሪው በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ መሆኑን ለማሳየት በከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ፤ በእሱም ልደት ለፍጥረት ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡

በነቢያት አፍ እርሱ የተናገረውን ለኛ ለሰዎች የሰጠውን የደኅንነት ተስፋ ለመፈጸም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በሥጋ በተገለጠ ጊዜ በሰማያውያንና በምድራውያን ሁሉ ዘንድ ታላቅ ደስታ ሆነ፤  የሰማይ መላዕክትም በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በማለት ደስታቸውን ገለጡ፡፡

“በድንገት ብዙ የሰማይ መላእክት ከመልአኩ ገር አብረው ታዩ፤ እግዚአብሔርንም በማመስገን፣ “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን.፣ በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን” ይሉ ነበረ፡፡” (ሉቃስ 2፡13-14)

ሐዋርያው ጳውሎስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ሰዎችን ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለማውጣትና ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመስጠት መሆኑን በመግለጽ በኤፌ 2፡14  “ለእናንተ ርቃችሁትና ቀርበው ለነበሩት ለእርሱም የምሥራች ቃል ስበክ” ብሎ ይናገራል ፡፡ የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ሰዎችን ከኃጢአታቸው ነፃ አድርጎ ፍፁም ደስታና ሰላምን ለመስጠት ነው፡፡ ስለሆነም በክርስቶስ ልደት በተገኘው የእኛ ከኃጢአት መዳን ከኃጢአት ባርነት ወጥተን የእግዚአብሔር ልጆች ለመባል ስለበቃን አምላካችንን ዘወትር ልናመሰግነውና ልናመልከው ይገባናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም ሲመጣ ለሰው ልጆች ሰላምን ለመስጠትና በኃጢያት የተበላሸውን ዓለም ለማደስ የዘመናት ሁሉ የሰላም አባት በመሆን ለሰው ልጆች ደኅንነት ተወልዶአል፤ እኛም በሙሉ ልባችን ተቀብለነዋል፡፡ እርሱ የዓለም ብርሃን ሆኖ የጠፋውን ዓለም ለማዳን የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ መጥቶአል፡፡

የሰው ልጆች በታላቅ ደስታ መኖር እንዲችሉ በክርስቶስ  ያገኘነውን ደስታ ሰላምና ነፃነት ፍፁምና ዘላዓለማዊ እንዲሆኑ እርሱ ለሰላም እንደጠራን እኛም ይህን ጥሪ ተቀብለን በእምነት ወደርሱ ልንቀርብ ይገባናል፡፡ ሁላችንም የሰላም አባት እንዳለን ሁሉ የሰላም ሰዎች በመሆን እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች እንሁን፡፡ ከህብረብሔሮች ወገኖቻችን ጋር አብረን እንደልማዳችን በሰላም፣ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመቻቻል እንኑር፡፡ ማኅበራዊ ኑሮአችንን በኅብረት በመምራት በአንድ ሀገር ልጆች መንፈስ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ልንኖር ይገባናል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ናት፤ እኛም ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ የሚያምርብን ኅብረታችን ነው፡፡

በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች ተከስተው ለነበሩ ገጭቶችና የዜጎች መፈናቀል እንደዚሁም የትምህርት መቋረጥ አስመልክቶ የሃይማኖት አባቶችና መንግስት ጉዳዩን ለማስቆምና ወደ ነበረበት ለመመለስ ስለ ሰላም የሚሠሩትን ሥራ አጠናክረው በመቀጠል ክቡርና ውድ የሆነውም የሰው ሕይወት ከጥፋት እንዲታደጉ፤  የአገራችን ዜጎችም ከተለያዩ ግጭቶች በመራቅ ኑሮአቸውን፤ ትምርታቸውንና የየዕለት ሥራ ክንውኖቻቸውን በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ መምራት እንዲችሉ የሃይማኖት አባቶች በየእምነታቸው ስለ ሰላም እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ መንግስትም እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በኢትጵያዊነት ባህልና ወግ ከህዝቦች ጋር በመወያየትና ለችግሮቹ መፍትሔ በመሻት ለሰላም መስፈን እንዲሰሩ ማስገንዘብ  እንወዳለን፡፡

“ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እነደሚሰጠው ዐይነት አይደለም፤ ልባችሁ አይጨነቅ፣ ደግሞም አይፍራ !”(ዮሐ. 14፡27)

       የተወደዳችሁ ምዕመናን !

የጌታን ልደት ሰናከብር ልንፈጽመው የሚገባን ትልቅ ክርስቲያናዊ ተግባር አለ፡፡ ይኸውም ሁሉም አቅሙ በፈቀደለት መጠን ድሆችን በመርዳት ምንም የሌላቸውን ምስኪኖች በማብላትና በማልበስ የበጎ ሥራዎችን በመፈጸም በዓሉን አክብረን እንድናሳልፍ አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በእርሱ ፍቅር እያደግን በእውነተኛ መንፈሣዊነት ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ሕይወታችንን ልንመራ ይገባናል፡፡ ክርስቶስ የሰላም ንጉሥ እንደመሆኑ በርሱ በኩል ለሚመጡትም ሰላምና ደኅንነት እንደሚሰጥ ተገንዝበን በእምነት ወደርሱ እንቅረብ ፡፡

የዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላካችን በፀጋውና በበረከቱ ለዓለም ሁሉና ለምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያ ምህረቱንና ሰላሙን ይላክልን ፡፡

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አገራችንን ለዘለዓለሙ

ይጠብቅልን  ይባርክልን !

 

+ ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *