“የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ…”

“የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ…”

ኅሊናና ጥበቡ ከቤተ ክርስቲያን ወጡ፡፡ የጰራቅሊጦስ በዓል የተከበረበት ቀን ነበር፡፡

ኅሊና፦ ዛሬ ልዩ ቀን ነው፤ የመንፈስ ቅዱስ በዓል ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ልደት ቀን። ሌሎች ታላላቅ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችን የምናከብርበት ቀን።

ጥበቡ፦ የትኞቹ ሥራዎች?

ኅሊና፦ እነሱም ታላላቅ ልደቶች ናቸው፤ አንዱ የጌታችን ልደት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ሥራም አይደል የተጸነሰው፤ ሌላው የዓለም ልደት ነው። “የእግዚአብሔር መንፈስ በውሃ ላይ ሰፍፎ ነበር” ይልም አይደል። የዓለምን ውብት ሳይ፣ ፈጣሪ መንፈስ እንዴት የውበትም ምንጭ እንደሆነ አስባለሁ፤ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሰጪ ነው።

ጥበቡ፦ እንዳልሽውም ዛሬ የቤተ ክርስቲያንንም ልደት እያከበርን ነው።

ኅሊና፦ እውነትህን ነው። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በቃል ተገልጾ አያልቅም።

ጥበቡ፡ – ጰራቅሊጦስ ማለት ግን ምን ማለት ነው?

ኅሊና፦ አጽናኝ፣ ጠበቃ፣ ማለት ይመስለኛል። ሌላም ማለት ይቻላል።

ጥበቡ፣ ለመጽናናት እኮ ኃዘን ነበር ማለት ነው፤ አይደለም?

ኀሊና፡- አዝኜ አላውቅም እንዳትለኝ ብቻ!

ጥበቡ፣ ኧረ ምን ማዘን ብቻ፤ ስቅስቅ ብዬም አልቅሼ አውቃለሁ። በሰቆቃም አልፌአለሁ።

ኅሊና፤ ከሁሉ የበለጠ ያሳዘነህ ነገር ግን ምንድነው?

ጥበቡ፣ በጣም የምወደው ሰው የሞትበኝ ጊዜ። በጣም ያመመኝ ጊዜም እንዲዚሁ ሆኛለሁ።

ኅሊና፣ ታዲያ በዚያን ጊዜ አልጸለይክም እንዴ?

ጥበቡ፣ በጣም ተማርሬ ነበርና፣ “ለምን! ለምን! አምላኬ ብዬ ጮኸኩኝ!” ይስማኝ አይስማኝ ግን አላውቅም። እንዳላስቀየምኩት እፈራለሁ። ማመስገን ሲገባኝ ያጕረመረምኩኝ ይመስለኛል።

ኅሊና፣ ስቃይንና ኀዘንን ለአምላክ መግለጽ ስሕተት ከሆነማ፣ የዳዊትና የነቢዩ ኤርምያስ ሰቆቃም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖር አልነበረባቸውም ማለት እኮ ነው። የመዝሙረ ዳዊት አንድ ሦስተኛው ለማለት ይቻላል፣ ከሰቆቃ ለመዳን የሚደረግ ልመና ወይንም የሰቆቃን ክብደት የሚገልጽ ጽሎት ነው።

ጥበቡ፣ ታዲያ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሰማ በምን እናውቃለን?

ኅሊና፣- ኤርምያስ በሰቆቃው መሃል ውስጥ ሳይቀር ለአምላክ ውዳሴ ያቀርባል። በመዝሙረ ዳዊትም ሰቆቃው ከተገለጽ በኋላ ውዳሴ ይከተላል። ይህም የመጽናናት አምላክ ማጽናናትንና ብርሃንን ወይም ተጨባጭ መልስን እንደሰጠ ያመለክታል።

ጥበቡ፤ የአልጋ ቁራኛ የሆነ ሰው እንዴት እንደሚጸልይ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው።

ኅሊና፣ እውነትህን ነው፤ ስንት ጊዜ ሳልረዳው ያመለጠኝ ነገር መሰለህ። በፊት በፊት በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ያሉት የኃዘን ጸሎቶች አይገቡኝም ነበር። እንዲያውም ብስለት የጎደለው ጸሎት ይመስለኝ ነበር። ግን ከጊዜ በኋላ ሰው ኃዘኑን ለአምላኩ መግለጹ ጤናማ ነገር መሆኑን የተረዳሁት። ቁስልን ለአምላክ ማሳየት ለካስ ምንም ነውር የለውም።

ጥበቡ፣ ነቢያትና ኢዮብ ብቻ ሳይሆኑ ክርስቶስም ኃዘኑን ገልጾአል። ለኢየሩሳሌምም ለአላዛርም አልቅሶአል። ጳውሎስም ከኃጢአት ሕይወት መላቀቅ እንዴት ከባድ መሆኑን ሲገልጽ “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ?” ብሏል።

ኅሊና፦ በነገራችን ላይ፣ አንድ መጽናናት የሚያሻት፣ የረሳናትና በጣም የምንበድላት እናት አለች እኮ!

ጥበቡ፦ እሷ ደግሞ ማን ትሆን?

ኅሊና፦ እስቲ ገምት፤ የመጀመርያዎቹ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጊዜ ነው የተወለደችው።

ጥበቡ፦ ወላጅ እናት ማለትሽ ይሆን? ግን ደግሞ እናታቸውን የሚያስታውሱ ልጆችም አሉ፤

ኅሊና፦ እናታቸውን የሚረሱ ልጆች ቢኖሩም፣ እኔ መጥቀስ የፈለኩት በተለይ ሁኔታ በደል ስለሚደርስባት እናት ነው። የሷ እንባና የድሆች እንባ ወደ ሰማይ ይጮኻል።

ጥበቡ፡ ድሆችን የምትወክል ነገር ናት እንዴ?

ኅሊና፦ “ድሃን የሚንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው፣ እሷንም የሚበድል ፈጣሪዋን ያስቀይማል። በአንዳንድ አገር ስለሷ ክብር ሁሌ ይነሣል። እሷ እናታችን ምድር ነች። የልደት በዓልም ሆነ የጋብቻ፣ የትምህርት ምረቃም ሆነ ልዩ ክብረ በዓል ሲከናወን ስለሷ ክብርና ፍቅር ዛፍ ይተከላል። እንዲያውም በልደት በዓል፣ በዓመቱ ቁጥር ልክ ነው ዛፍ የሚተከለው።

ጥበቡ፦ የሚገርም ባሕል ነው። በበዓል ዛፍ መትከል!

ኅሊና፦ ሁሉም ቢያደርገው እንዴት ጥሩ ነበር፤ ግሩም ባሕል አይደለም እንዴ!

ጥበቡ፦ ባንድ ወገን ንሥሐ፤ በሌላ ወገን ለፈጣሪ መንፈስ ቅዱስ ልመና ልናቀርብ ይገባናል። አጽናኙ መንፈስ ድሆችንና የተበደለችውን ምድር እንዲያጽናና።

ኅሊና፦ እውነት ነው። ምድር እየተሰቃይች ነው። ከበፊቱ የበለጠ የተሰቃየችው በሰው ልጆች ስግግብነትና ትዕቢት ነው። ሰው ለራሱ ብቻ የሚያስብ ፍጡር ሆነ።፡ዳሩ ግን፣ ከአፈር እስከተፈጠርን ድረስ የምድርና ሞላዋ ዘመዶች እኮ ነን። የኢዮብ መጽሐፍ ምን የመሰል ትሕትና እንዲኖረን ያስተምረናል። በመጽሐፉ መጨረሻ እግዚአብሔር ስለ ፍጥረታት የሚናገረውን ማስተዋል ያሻል። ኢዮብ ያላየውን ዓለም መቃኘት ቻለ፤ ታዲያ ሰው ማስተዋል ያቃተው ምድር ስተበደል፣ ድርቅ፣ ስደትና ጦርነት እንደሚበዛም ነው።

ጥበቡ፦ ሰው ባላደራ መሆኑን ረስቶ እንደፈለገ ምድርን ስለበዘበዘም አይደል። ታዲያ ምን እናድርግ። ዛሬ በበዓል ቀን ዛፍ እንዳንተክል አይመችም። ነገ ብንተክልስ?

ኅሊና፣ ነገ፣ ለምን ነገ! ዛፉን መሸት ሲል እንትከል። ተክልን ምድርን ብናጽናናት ምን አለ? አሁን ድግሞ የታመመን ወይም ያዘነን፣ ወይንም የተሰደደን ብናጽናና የአጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእኛ እንዲሠራ ፈቀድን ማለት ይመስለኛል። አሁን የታመመ ሰው ብንጠይቅስ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *