“በአንተ ብርሃን ብርሃንን እናያለን”

አባ ዳንኤል አሰፋ

(ከካፑቺን ፍራንቸስካውያን የምርምርና የጽሞና ማዕከል)

የፋሲካ በዓል ተቃርቦአል። ኅሊናና ጥበቡ ከበዓሉ በፊት ታሪካዊና መንፈሳዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ወሰኑ። በዚህም መሠረት ክርስቲያኖች ይጸልዩበት ወደ ነበር ወደ አንድ ዋሻ ሄዱ። ዋሻውን የሚጎበኙ ሰዎች በደንብ መዘጋጀት ያስፈልጋቸዋል። ለመራመድ የሚመች ጫማ፣ ጎንበስ ቀና ለማለት የሚመች ልብስና መብራት የግድ ያስፈልጋሉ። ጥበቡና ኅሊናም በሚገባ ተዘጋጅተው ዋሻ ውስጥ ገቡ።

ጥበቡ፦ በታፈነና በጠመዝማዛጨለማ ዋሻ ውስጥ ማለፍ ይከብደኛል። ቶሎ በወጣን!

ኅሊና፦ ጨለማ አትወድም ማለት ነው። ሳይበዛ በመጠኑ ቢኖር እኮ የሚጎዳ አይመስለኝም።

ጥበቡ፦ ኧረ እኔ በመጠኑም ቢሆን አልፈልግም። ምን ጥቅም አለው ብለሽ ነው?

ኅሊና፦ ቢያንስ ብርሃን ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ለማስተዋል ይረዳሃል። በዚህ ላይ፣ወደ እግዚአብሔር ምሥጢርም ሲገቡ በጨለማ ማለፍ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ሙሴም እኮ ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ፣ በተራራ ላይ ከአምላኩ ጋር ተነጋግሮአል።

ጥበቡ፦ እንደ እውነቱ ከሆነ ጨለማና ዋሻ ሞትን ያስታውሱኛል።

ኅሊና፦ ታዲያ መዝሙረኛው፣ “በሞት ጥላ ውስጥ እንኳን ባልፍ፣ አንተ ከኔ ጋር ነህና አልፈራም፤” ብሏል እኮ! እንዲሁም፦ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ይላል።

ጥብቡ፦ ትልቅ ጥቅስ ነው የጠቀስሽው። ሞትና ጨለማ ያስፈራሉ። ምን እንደሚሆን፣ ወዴት እንደምንሄድ አለማወቁ እራሱ ያስፈራል። ነገር ግን በዚህ ሁሉ “አንተ ከኔ ጋር ነህ” ማለት ትልቅ የእምነትና የተስፋ ምስክርነት ነው።

ኅሊና፦ አየህ! ጥበቡ፣ ተመለስ! ተመለስ!

ጥበቡ፦ ምን አለ? ምን አየሽ! ከፊት አደጋ አለ እንዴ?!

ኅሊና፦ አይ፤ ከፊት ያየሁት አደጋ የለም። ይልቁንም ሳናስተውላቸው ልናልፋቸው የነበሩ ስዕሎች ናቸው ትኩረቴን የሳቡት። በግራና በቀኝ በኩል ግድግዳው ላይ የተሳሉትን ስዕሎች አየህ?

ጥበቡ፦ ሰዎች ጥለውን እየሄዱ ነው፣ ብንከተላቸው አይሻልም።

ኅሊና፦ ተመልከት ይህ ስዕል እንዴት ያምራል! ሳናየው ከሄድንማ፣ ጉብኝታችን ሙሉ አይሆንም።

ጥበቡ፦ በይ እሺ፣ የምናይ ከሆነ፣ በደንብ አስተውለን እንድንመለከት በቂ ብርሃን ላዘጋጅ።

ኅሊና፦ ይህ ስዕል፣ በዮሐንስ ወንጌል፣ ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ታሪክ ያመለክታል።

ጥበቡ፦ ምን ይሆን ለመግለጽ የተፈለገው?

ኅሊና፡ ሰውየውና የዓለም ሰዎች ተሳስረዋል። ሰውየው የኛን የሰው ልጆችን ሁኔታ የሚወክል ይመስላል።

ጥበቡ፦ የሰው ልጅ ሁኔታ በጨለማ ተመሰለ ማለትሽ ነው?

ኅሊና፦ አዎን፤ ግን ታሪኩ እንዲህ አያልቅም። በብርሃን የሚመላለሱ ሰዎችም አሉ። እንዲሁም ወደ ብርሃን የሚጓዙ ሰዎችም በስዕሉ ላይ ይታያሉ።

ጥበቡ፦ የጥምቀት ምልክትም ይታየኛል። ሰውየው ተጠመቀ ማለት ነው እንዴ?

ኅሊና፦ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ሞቶ ከክርስቶስ ጋር መነሣት፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገር ማለትም አይደል።

ጥበቡ፦ እኽ…

ኅሊና፦ ሰውየውም ወደ ብርሃን በመምጣቱ፣ ለጥምቀትም ምሳሌነት ያገለግላል።

ጥበቡ፦ እንዴት?

ኅሊና፦ ሰውየው ሲጀመር ኢየሱስን አያውቀውም ነበር። “ኢየሱስ የሚባል ሰው ጭቃ በዓይኔ ላይ አድርጎ ታጠብ አለኝ፤ እኔም ማየት ቻልኩ”፤ አለ። ቀስ በቀስ ግን ለሚጠይቁት ሰዎች “ኢየሱስ፣ ነቢይ፣ የእግዚአብሔር ሰው” መሆኑን ይናገራል። በመጨረሻም፣ በኢየሱስ አምላክነት አምኖ እፊቱ ይሰግዳል። ባንድ በኩል፣ ሥጋዊ ዓይኑ ተገልጦ የፍጥረታትን ውበት ይቃኛል። በሌላ በኩል፣ መንፈሳዊ ወይም ውስጣዊ ዓይኑ ተገልጦ በክርስቶስ ውበት ይዋጣል። ሁለት ጊዜ ዓይን መገለጥ። አዲስ ፍጥረት መሆን! ታዲያ ለጥምቀት ጥሩ ምሳሌ አይሆንም?

ጥበቡ፦ ይገርማል። ይህንን ስዕል ፎቶ ላንሣው። ጥሩ ማስታወሻና ማስተማርያ ይሆነኛል። ስለ ጥምቀት የሚያብራራ ስዕል።

ኅሊና፦ ጥሩ ሐሳብ ነው። ገና ብዙ ሊያወያየን ይችላል። ብርሃን፣ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብዙ ምሥጢር አለው። የዓለም ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ለዓይን ስውሩ ብርሃንን ሰጠው። “እናያለን፣ እናውቃለን፣ ብርሃንም ሆነ አስተማሪ አያስፈልገንም” የሚሉት ደግሞ በጨለማ ቀሩ።

ጥበቡ፦ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” የሚለውን እንዴት ትረጂዋለሽ። ኢየሱስም፣ እኛም እንዴት ብርሃን እንሆናለን?

ኅሊና፦ ኢየሱስ ያልተፈጠረ ብርሃን ነው። የብርሃን ምንጭ ነው። እኛ ፍጡራን ነን። ነገር ግን የብርሃን ማስተላለፍያ መሆን እንችላለን። ፀሐይና ጨረቃም ብርሃን የሚሰጡት አምላክ እንዲህ አድርጎ ስለፈጠራቸው ነው።

ጥበቡ፦ የዓይነ ስውሩ ሰው መፈወስ ለኛም መፈወስ ምሳሌ መሆን አይችልም?

ኅሊና፦ በሚገባ፤ በብዙ ነገር እንታወራለን። በአመለካከት፣ አርቆ ባለማሰብ፣ በራስ ወዳድነት፣ በስግብግብነት፣ በትዕቢት፣ በቅናት፣ በምቀኝነትና በመሳሰሉት እንታወራለን። ዋናውና ድቅድቁ ጨለማ ይኼኛው ጨለማ ነው።

ጥበቡ፦ የእግዚአብሔር ቃል ሲፈውሰን፣ ጨለማው ተገፎ በአዲስ መልክ ማየት እንጀምራለን ማለት ነው።

ኅሊና፦ አዎን፤ የእግዚአብሔር ቃል መድኃኒትም፣ ብርሃንም ነው። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ዘንድ ጨለማ የለም፤ ሌሊቱም እንደ ብርሃን ነው።

ጥበቡ፦ ‹‹በብርሃንህ ብርሃንን›› እናያለን  የሚለው ጥቅስ (መዝ 36፡9) ይህንን ምሥጢር ይገልጽ ይሆን?

ኅሊና፦ እውነትህን ነው፣ ቃሉን ለማንበብና ለመረዳት ብርሃን ያስፈልገናል። በቃሉ ብርሃን ቃሉን እንረዳለን…

ከዋሻው ከወጡ በኋላ ተመስጠው ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ የፋሲካ ሌሊት ደረሰ። ምእመናን ጧፍ ይዘው፣ ከዑደት በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመራሉ። ኅሊናና ጥበቡም ከምእመናን መሀል ነበሩ። በጌታ ብርሃን፣ የትንሣኤን ብርሃን ለማክበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *