የጥበብ መጀመርያ

“የጥበብ መጀመርያ…”

“ምነው ተከዝክ ጥበቡ?” አለች ኅሊና።

“የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚለው ጥቅስ ነው የሚያስተክዘኝ፤ አለ ጥበቡ።

“በዚህ አልስማማም እንዳትለኝ ብቻ”፣

“ኧረ በጭራሽ”፣

“ታድያ ምን እያሰብክ ነው?”

“‘ጥበብ’ የሚለው ቃል ተስማምቶኛል፤ ‘መፍራት’ የሚለው ቃል ግን፣ እንዲያው ያስፈራኛል”፣

“መፍራት ሲባል፣ መንቀጥቀጥ፣ መደናበር፣ መሸበር ማለት እንዳይመስልህ”፤

“ታዲያ ምን ማለት ይሆን”?

“እንደዚያ ካሰብክማ፣ መተከዝህም ሆነ መፍራትህ አያስደንቀኝም፤” አለች ኅሊና።

“እግዚአብሔርን መፍራት ልዩ ምሥጢር አለው እያልሽ ነው እንዴ?”

“በሚገባ፣ ጥበቡ፣ ልዩ ምሥጢር አለው። እስቲ አንድ ታሪክ ላጫውትህ፤

በአንድ ከተማ የሚኖር አንድ ባለ ሀብት ነበር። አንድ ጊዜ ስለ ዘላለም ፍርድና ስለ ዘላለማዊ ቅጣት የሚያወሳ መጽሐፍ ሲነበብ ይሰማና እጅጉን ይደነግጣል። ከመረበሹም ብዛት፣ ንብረቱን ሸጦ ወደ አንድ ገጠር ይሄዳል፣ እየጾመና እየጸለየ መኖር ይጀምራል። ነገር ግን ለብዙ ዓመታት በእንዲህ ሁኔታ ቆይቶም ፍራቻው፣ ድንጋጤው አልተው ይለዋል። ጸሎቱም እየሰለቸው ይሄዳል። ደስታም እንደራቀው ይቆያል። በጥርጣሬም ይዋጣል። ከዕለታት አንድ ቀን አንድ መንፈሳዊ ሰው ያገኘውና ለምን እንደተከዘ ይጠይቀዋል። እርሱም ታሪኩን በዝርዝር ይነግረዋል። ያም መንፈሳዊ ሰው እንዲህ ሲል ይመልሳል። “ድካምህ ሁሉ ያሳዝነኛል። ነገር ግን በሕይወትህ ምርጫ ላይ ሁለት ችግር አያለሁ፤ አንዱ በፍቅር ተነሣስቶ መድከምና ከፍራቻ የተነሣ መድከም ልዩ መሆኑን የተረዳህ አይመስለኝም። ፍራቻ ፍቅርን አይወልድም። ለዚህም ነው ጸሎት እየሰለቸህ የመጣው፤ ፍራቻ ነጻ አያደርግም፤ ወንጌል ግን ስለ ነጻነት ነው። በፍራቻ ማገልገልና በፍቅር ማገልገል አይገናኙም። ሌላው ደግሞ ሽልማት ብቻ ፈልጎ እግዚአብሔርን ማገልገል የተቀጣሪን ወይም የጥቅም ፈላጊን መንፈስ እንደ መላበስ ነው። ለመሆኑ እግዚአብሔርን ነው የምትፈልገው ወይንስ የምታገኘውን ጥቅም? ከሁሉም የሚበልጠው ሽልማትህ እግዚአብሔር እራሱ ነው ወይንስ በሩቅ ሆነህ ከእርሱ የሚገኘውን ነው የምታስበው? እግዚአብሔር ካንተ ጋራ መሆኑን ነው የምትመኘው ወይንስ ትኩረትህ በሙሉ ስለ ራስህ መጠቀም ብቻ ነው? አማኑኤልን ነው የምታስበው ወይንስ እራስህን ብቻ። ስለሌሎች መዳን ነው የምትጸልየው ወይንስ ስለ ራስህ ብቻ?”

ሰውየው ለእነኚህ ጥያቄዎች ምንም መልስ መስጠት አልቻለም። ነገር ግን በመገረም ፈዞ ቀረ። ትንሽ ቆይቶ፣ “ታዲያ ጊዜዬን አባከንኩ ማለት ነው!?” አለ። መንፈሳዊውም ሰው “ቁም ነገሩ አዲስ ብርሃንን ማግኘትና ብርሃኑን መቀበሉ ላይ ነው። በጉዞህ ላይ ሁሌ ተማሪ መሆንህን አስታውስ። ካለህበት ተነሥተህ ወዴት መሄድ እንደምትችል አስብ እንጂ ባለፈው ተቆጭተህ እስረኛ አትሁን፤ ውስጥህ በፍቅር ቢሞላ፣ ለጥርጣሬ ቦታ አይኖርም፣ ሰላምም ታገኛለህ” አለው።

ጥበቡም በተመስጦ ካዳመጠ በኋላ፦ “የሚገርም ታሪክ ነው የነገርሺኝ፤ ሆኖም እግዚአብሔር ባለ ግርማና እጅግ አስፈሪ መሆኑን መርሳት እንችላለን እንዴ?” አለ።  እንደሱ ማለቴ አይደለም። የእግዚአብሔር ግርማና ኃይል እኛ ልናስበው ከምንችለው በላይ ነው። ለዚህም ቃላት የለንም። በፍጡርም አእምሮ የምንደርስበት አይደለም። ሆኖም መደንበርና እግዚአብሔርን መፍራት ልዩ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፤ የእስራኤል ሕዝብ ባሕሩን በሚሻገርበት ወቅት የፈርዖን ሠራዊት ሲመጣባቸው ተሸበሩ (ዘጸ 14፡ 10)፤ ፈርዖንን ፈሩት እንጂ አልወደዱትም፣ ሸሹት፤ በአንጻሩ ያዳናቸውን እግዚአብሔር ፈሩ፣ ወደዱ፣ አከበሩ፤ በጌታ አመኑ (ዘጸ 14፡ 31)።  ሌላው ድንቅ ነገር ግን የክርስቶስ መልካም ዜና ነው። በበረት የተወለደው ሕጻን ‘አትፍሩ፣ እያለ አይደለም እንዴ? መቼም ሕጻንን የሚፈራና የሚሸሽ ያለ አይመስለኝም። ይኸው ታላቁ የገና ምሥጢር!”

“ታዲያ ኢዮብ እግዚአብሔርን ይፈራ ነበር ተብሎ ተጽፎ የለምን” አለ ጥበቡ።

“ትክክል” አለች ኅሊና፣ የኢዮብ ትልቅነት ቢመቸውም ባይመቸውም እግዚአብሔርን ማክበሩ ላይ ነው። የሰይጣንም ፈተናና ክስ እኮ ይህ ነበር፤ ማለትም፣ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው ጥቅም ስላገኘ ብቻ ነው፤ ጥቅሙን ቢያጣ እግዚአብሔርን ይሰድባል። (ኢዮብ 1፡ 9)። ዳሩ ግን፣ ኢዮብ ንብረትና ጤና ባጣበትም ወቅት እግዚአብሔርን አከበረ። በመጨረሻም እግዚአብሔር ኢዮብን ይደግፈዋል፤ የኢዮብን ወዳጆች ግን ይወቅሳቸዋል።

“ታዲያ ጌታን የሚፈራ ማለት ጌታን የሚያከበርና የሚወድ ማለት ይሆን?” አለ ጥበቡ።

“መውደድ ማክበርም ስለሆነ፣ እንደዚያ ማለት የሚቻል ይመስለኛል፣ ስንቴ ነው ‘አትፍራ’፣ ‘አትፍሪ’ የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናነበው? እግዚአብሔር ሰዎችን ለዓላማው ሲጠራ፣ ሰዎችም ፈርተው ‘ይህ ተልእኮ ከባድ ነው፣ እኔ አልችለውም’ ሲሉ ‘አይዞህ፣ አይዞሽ፣ እኔ ካንተ ጋር ነኝ፣ ካንቺ ጋር ነኝ’ ይላል፡ አለበለዚያ፣ ‘አባታችን ሆይ’፣ ብሎ መጸለይ ምን ትርጉም አለው? ‘የልጅነት መንፈስ’ ተቀበልን ማለትስ? በፍጹም ፍቅር ውስጥ ፍርሃት የለም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ተብሎ እንደተጻፈው።” አለች ኅሊና።

“እኔ እኮ ግን የሰጋሁት፣ ሰው ፍርሃት አያስፈልግም ብሎ፣ የባሰ ደፋር ይሆንና፣ ከመስመር እንዳይወጣ ነው፤ ዐመፀኛም እንዳይሆን ነው”። አለ ጥበቡ።

“ከፍራቻ ይልቅ እኮ ፍቅር ጥሩ መካሪ፣ ታላቅም ገሪ ነው። መለኮታዊ ፍቅር ተአምር ይሠራል።” አለች ኅሊና።

ጥበቡ መጻሕፍትን ያገላብጣል። ከመመሰጡም ብዛት ኅሊና ወደ እርሱ መቅረብዋንም አላስተዋለም ነበር። “እንደምን አረፈድክ?” ስትለው ነው ሰው አጠገቡ መኖሩን የተገነዘበው። በታላቅ ፈገግታ “እንደምን አረፈድሽ፣ ኅሊና?” አለ። ከተቀመጠበት ተነሥቶም ወንበር አቀረበላትና ውይይታቸውን ጀመሩ፤

“ዛሬ ደግሞ ምን እያጠናህ ነው? ምንድነው እንዲህ የመሰጠህ?” አለች ኅሊና።

“ይኼ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ነው ትኩረቴን የሳበው፤” አለ ጥበቡ።

“ድንቅ ነው፤ ታዲያ ምን አዲስ ነገር ተማርክ?”

“ግራ ስለገባኝ ነገር ብነግርሽ አይሻልም?”

“ምንድነው ግራ ያጋባህ?”

“ሲጀመር ‘ባልንጀራ የሚለው ቃል አልገባኝም።

“እሱማ፤  እንጀራን አብሮ የሚቆርስ፣ዐብሮ አደግ፣ ወዳጅ፣ ማለትም አይደል?”

“ታዲያ ጥያቄው፣ ሊወደኝ የሚገባው ሌላ አይሁዳዊ ነው ለማለት ይሆን?” አለ ጥበቡ።

“አዎን እንደዛ ማለቱ ይመስላል፤ ነገር ግን የክርስቶስ ፍቅር ሌላም ገጽታ ይጨምራል።”

“ምን ማለትሽ ነው? እስቲ አብራሪው።”

“ይኸውልህ፣ ከኢየሱስ ጋር ይነጋገር የነበረው የሕግ መምህር፣ ሲጀመር ዓላማው ስለዘላለም ሕይወት መንገድ ማወቅም ሆነ ስለ ባልንጀራ መረዳትም አልነበረም። ዓላማው ወጥመድ መዘርጋት ሲሆን፣ የተገፋፋውም በትዕቢት ነው። ወዳጁን መምረጥና መወሰን ፈለገ። በሱ መለኪያ ሮማዊ፣ ግሪካዊ ወይም ሳምራዊ ወዳጁ ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ ግን ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም። ‘ሰዎችን በዘር በቀለም ሳትለይ ለወዳጅነት ምረጥ’ አላለውም። ይልቁንም አንድ ምሳሌ ተረከ። በምሳሌውም፣ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲሄድ በወንበዴዎች ተደበድቦ ለሞት እንዳጣጣረና አንድ ሳምራዊ ሰው እንዴት እንደረዳው ይናገራል። ቁስሉን አክሞ፣ ከወደቀበትም አንስቶት ወደ ማረፍያ ቦታ ይወስደዋል። የወደቀውን ሰው ከሳምራዊው በፊት አንድ ካህንና አንድ ሌዋዊ አይተውት ነበር። ነገር ግን አልደረሱለትም። ወደ ሰውየው ከመቅረብ ይልቅ መራቅን መረጡ። ባልንጀራ አልሆኑለትም።

“መቼም ይህ ምሳሌ የሕግ መምሕሩን ሳይረብሸው አልቀረም፣ አይደል? አለ ጥበቡ።

“እንዴታ፣ በጣም ይረብሸዋል እንጂ! ለሱ እኮ አንድ ሳምራዊ የመልካም ሥራ አርአያ መሆን አይችልም! ባይሆን፣ ሳምራዊው ከደብዳቢዎቹ መሃል ቢሆን የሚጠበቅ ነገር ነው ብሎ ሳያስብ ይቀራል?”

“ታዲያ ኢየሱስ ባልንጀራ ለሌላው የሚደርስና የሚያዝን ነው ማለቱ ነዋ?”።

“ትክክል ብለሃል፤ ባልንጀራህ የአንተ ማኅበር፣ ሃይማኖት፣ ብሔር አባል መሆን አይጠበቅበትም። ለዚህ ለወደቀው ሰው ያዘነለት ሳምራዊ ዘመዱ አልነበረም። ሳምራዊው የረዳበት የተደበቀ ምክንያትም አልነበረውም፤ ልርዳውና በኋላ እሱም ይጠቅመኛል አላለም። ርኅራኄ ብቻ ነው የገፋፋው።” አለች ኅሊና። ስትቀጥልም፣ “በዛሬ ዘመን ስለተከሰተ ነገር ላጫውትህ” አለችው።

“አንዲት ነጭ ወጣት ተማሪ ነች የነገረችኝ። ለእረፍት ወደ አንድ ሩቅ አገር ትሄዳለች። እዚያም ያገሯ ሰዎች ይጠብቋታል። የሚቀበሏት ሰዎች ጥቁሮች እንዳሉና ሰው እንደማያከብሩና አደገኛም እንደሆኑ ነግረዋታል። በፍጹም በመኪናቸው ውስጥ እንዳትገቢም ተብላለች። ያጋጣሚ ነገር ሆነና አድራሻ ትሳሳትና የወሰደችው የከተማው ባቡር ወዳልሆነ ቦታ ወሰዳት። ተሳፋሪዎችም እየወጡ እርሷ ብቻዋን ቀረች። ወደ ሹፌሩ ተጠጋች፤ ጥቁር መሆኑን ስታውቅ ደነገጠች። ስትፈራ ስትቸር ትክክለኛውንም አድራሻ በወረቀት ላይ ጽፋ አሳየችው። ካሁን ካሁን ገላምጦ ዞር በይ ይለኛል ስትልም ወደምትፈልገው ቦታ ለመድረስ የአንድ ሰዓት የመኪና መንገድ እንደሚጠይቅ ይነግራታል። መምሸቱን እያሰበች ትደነግጣለች። እንባዋ ይመጣል። የሚደርስላት ባልንጅራ ይኑር አይኑር አታውቅም። ሰውየው ግን ሐዘንዋን ተመልክቶ አረጋጋት። ሥራ እንደጨረሰ፣ ወደ ቤቱም በራሱ መኪና እንደሚገባ፣ ነገር ግን ወደምትፈልገው ቦታ ሊያደርሳት ፈቃደኛ መሆኑን ነገራት። አሁንም እየፈራች ወደ መኪናው ገባች። የተነገራት በፍጹም እነዚያ ሰዎች መኪና ውስጥ መግባት አደገኛ እንደሆነ ነበር። ሰውየው ወዳጆቿ በራፍ ላይ ሲያደርሳት ፍርሃቷ ወደ መረጋጋት፣ ኃዘኗ ወደ ደስታ ተለወጠ። ለማመስገን ብላ የነዳጅ ገንዘብ ለመክፈል ጠየቀች። ሰውየው ግን ገንዘብ እንደማይቀበል ነግሮአት በፈገግታ ሸኛት። እውነተኛ ባልንጀራ ሆናት።

“እንዴት የሚገርም ታሪክ ነው ባክሽ፤ ለካ በዘመናችንም ደጉ ሳምራዊ መሆን ይቻላል!”፣ አለ ጥበቡ።

“እንዴታ፤ አለች” ኅሊና።

ጥበቡም “አሁን፣ ሳስብ እኔም አንድ ነገር ትዝ አለኝ” አለና በተራው የሚከተለውን ነገራት፦ “በጦር ሜዳ አካባቢ በጥቁሮች አገር፣ በፈንጂ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡና የቆሰሉ ሕፃናት ነበሩ፤ ታዲያ ከእነኚህ አንዱን የአካል ጉዳተና ሕፃን አንዲት ነጭ ሴት ልታሳድገው ወሰደችው። እንደ ወላጅ እናት አፈቀረችው። ለልጁ ከማንም በላይ ደረሰችለት”። ጸጥታ ሰፈነ፤ ሁለቱም ተክዘው ቀሩ። ሰዓት ማለፉም አልታወቃቸውም።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *