ውኃ አጠጭኝ የሚልሽን ብታውቂው ኖሮ

“ውኃ አጠጭኝ የሚልሽን ብታውቂው ኖሮ…”
አባ ዳንኤል አሰፋ
(ከካፑቺን ፍራንቸስካውያን የምርምርና የጽሞና ማዕከል)
ኅሊናና ጥበቡ ጉብኝታቸውን ቀጥለዋል። በአንዲት የገጠር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሳምራዊቷን ሴት ታሪክ የሚገልጽ ስዕል በማድነቅ ላይ ናቸው።
ጥበቡ፦ ይህ ታሪክ በጣም ነው የሚስበኝ። በተለይ የሚገርመኝ ይህ ጥያቄ ነው፣ ‘አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን እንዴት ውኃ አጠጪኝ ትላለህ?’፣‘አንተና እኔ ምንም ግንኘኑነት ሊኖረን አይገባም’ማለቷ እኮ ነው። እኔና አንቺም እንዲህ ብናስብ ኖሮ ባልተነጋገርን ነበር። አስተዳደጋችን ልዩ፣ ብሔራችን ልዩ…
ኅሊና፦ እውነትህን ነው። አሳዛኝ ሁኔታ ነው። በዚህ ላይ፣ የውኃጉድጓድ ልዩ ምሥጢር ይኖረው ይሆን?
ጥበቡ፣ ከውኃ መቅጃ ምን የተለየ ትርጉም ይኖረዋል ብለሽ ነው?
ኅሊና፦ ሌላ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር የኢየሱስ ጥያቄ ነው። እርዱኝ ማለት እንዴት ከባድ እንደሆነ ይገባኛል። በተለይም ከሚንቁት ወገን የሆነ ሰውን እርዳታ መጠየቅ ከባድ ነው።
ጥበቡ፦ ኧረ ከናካቴው እርዱኝ ማለት የሚያሳፍራቸው ሰዎች አሉ።
ኅሊና፦ በእርግጥም በጉድጓድ አጠገብ ስለመቀመጥ ወይም ስለመገኘት ሲተረክ፣በሐሳብ ወደ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች መንጐዳችን አይቀርም። ልክ እንደ አብርሃም አገልጋይ፣እንደ ያዕቆብ ወይም እንደ ሙሴ፣ ኢየሱስም ወደ ባዕድ ሀገር መጓዙን ወንጌላዊው ዮሐንስ ይነግረናል።
ጥበቡ፦ የአብርሃም አገልጋይ ለይስሐቅሚስትለማምጣት ነበር ወደ ባዕድ ሀገር የሄደው።
ኅሊና፦ ያዕቆብ በበኩሉ ከወንድሙ ከዔሳው ለማምለጥ ሲል ነው ወደ አባቱ ዘመዶች ሀገር የሄደው፤ ሙሴም በበኩሉ ከፍርዖን ለማምለጥ ወደ ሚዲያም ሀገር ሸሽቶ ነበር።
ኅሊና፦ በእያንዳንዳቸውም ታሪክ ውስጥ ውኃ ፍለጋ ወደ ጉድጓድ ስለምትመጣ ወይም ስለሚመጡ ሴቶች ይገለጻል።
ጥበቡ፣ በእያንዳንዱ ታሪክ ውስጥም በወንዱ እገዛ ሴቲቱ ወይም ሴቶቹ ውኃ ይቀዳሉ፤ በአንዳንዶቹ ታሪኮች ደግሞ ውኃው ለወንዶቹ ነው የሚቀዳው።
ኅሊና፦ ከዚያም ሴቲቱ ወይም ሴቶቹ በሩጫ ወደቤት ሄደው አንድ እንግዳ መምጣቱን ያበሥራሉ። በመጨረሻም ድግስ፣ በእንግዳውና በሴቲቱም መሀል መተጫጨት ይከተላል።
ጥበቡ፡ ነገር ግን የኢየሱስና የሳምራዊቷ ታሪክ ከሌሎቹ ታሪኮች ይለይ የለምን?
ኅሊና፦ አዎን፣ ሰብአዊ ፍቅርን የሚሻጘር ጠለቅ ያለ መልእክት ያስተላልፋል።
ጥበቡ፣ በባሕል ጉድጓዱ የፍቅር መመሥረቻ ሥፍራ መሆኑ ነው፤ በዮሐንስ ወንጌል ግን የሕይወት ምንጭ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ፍቅር ነው የተበሠረ። መተጫጨትም ማለት ሙሽራውን ክርስቶስን ማወቅና ማመን መሰለኝ።
ኅሊና፦ በእውነቱ በዚህች ሳምራዊት ሴት ሕይወት ውስጥ የሚፈጠረው የሚደንቅ ነው። አንድ የማታውቀው አይሁዳዊ ያነጋግራታል።የሚጠይቃትም በወቅቱ ከነበረው የሃይማኖትና የባሕል ሥርዓት አኳያ ፍጹም እንግዳ ነው። በእርሷ ወገኖችና በኢየሱስ ወገኖች፥ በሳምራውያንና በአይሁድ መካከል አጥር እንዳለ ነው የምታውቀው። ግዙፍ፣ የሚጨበጥ አጥር ባይሆንም፥ እውን የሆነ ምናባዊ አጥር። እንዲያውም በግንብ ከተሠራ የሚጠነክር አጥር ነው ለማለት ይቻላል። ለምን ቢባል በግንብ የተሠራው አጥር ምንም ቢጠነክር በሰዎች ሊፈርስ ይችላል። እድሜው አጭር የሆነ አጥር ነው። ምናባዊው አጥር ግን በቀላሉ የሚፈርስ አይደለም። ክፍለ ዘመናትን ያቋርጣል።
ጥበቡ፣ በእርግጥም ሳምራዊቷ ሴት ከአይሁዳዊ ሰው ጥያቄ አትጠብቅም ነበር። አይሁዳዊም ከሳምራዊ ምንም አይጠብቅም። ለብዙ ዘመናት ሲወርድ ሲወረድ የመጣ ልማድ ነው ይባላል እንጂ ‘ልማዱ ትክክል ነው ወይ’ ብሎ የሚጠይቅ ያለ አይመስልም።
ኅሊና፣ ኢየሱስ ግን ልማዱ ስሕተት መሆኑን በተግባር አሳየ። ምናባዊውን ግንብ ንዶ መነጋገር ጀመረ።
ጥበቡ፣ ጳውሎስም የኢየሱስን ፈለግ ይከተላል። አይሁዳዊ ሆኖ ሳለ አይሁዳዊነቱን መኩሪያ፥ መመኪያ አላደረገውም። ‘የተመረጠ ሕዝብ አባል’ ነኝ ብሎ አልኮራም። ስለ ክርስቶስ ሲል፥ የሚያኮሩ የሚባሉትን ነገሮች ሁሉ እንደ ጥራጊ ቆጠራቸው እንጂ። በግሪክ የጥበብ ዓለም ውስጥ ቢያድግም በዚያም አልተመካም። ከዓለም ጥበብ ይልቅ በመስቀል ፍቅሩን የገለጸውን ጥበብ መረጠ እንጂ። የሮማዊ ዜግነት ቢኖረውም፣ ከሮማውያን እምነት ይልቅ ክርስቶስን አስበልጦአል። በዚህም የተነሣ ሮማውያን አንገቱን ሰየፉት። ማንነቱ በአባልነቱ እንደማይወሰን፣ ይልቁንም ከአባልነቱ እንደሚሰፋ አሳየ።
ኅሊና፦ አሁንም ኢየሱስ፦ ‘ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ፣አንቺ ትለምኝው ነበር፣ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር’ አላት። በተደጋጋሚ የኢየሱስ መልሶች ከምትጠብቀው በላይ ነበሩ። እሷ ስለምታስበው ሳይሆን ስለሌላ ውኃ ነው የሚገልጽላት።ለዘላለም የሚያረካ ውኃ! ጥልቁን የሰው ልጅ ጥም የሚቆርጥ ውኃ! የዚህ ስጦታ ባለቤት የሆነው ጌታ እያነጋገራት ነው። ምንኛ እድለኛ ነች? እንደማንኛውም ቀን ውኃ ልትቀዳ መጣች፤ የዚያን ዕለት ግን የሕይወት ውኃ ባለቤት የሆነውን አገኘችው! የማይንቃትን፣የማይፈርድባትን ጌታ አገኘች። የግልታሪኳን የሚያውቅ፣ነገር ግን ሳይከሳት ስለ እግዚአብሔር ስጦታ የሚያበሥራትን ጌታ አገኘች።
ጥበቡ፦ ኧረ ሰዎቹ ሁሉ ጥለውን ሄዱ። ኧረ እንከተላቸው! ምንም የሚታይ ሰው የለም። ብቻችንን ቀረን።
ኅሊና፦ አየኸ፣ በዚህ ስዕል ምክንያት ብዙ ተወያየን። ውኃ የት ይሆን የምናገኘው? በቂ ውኃ ባለመያዛችን ልንጎዳ ነው። በጣም ነው የጠማኝ።
ጥበቡ፦ ቦታው ቆላማነው። ከዘነበም የቆየ ይመስላል። በአቅራቢያውም ምንጭ ይኑር አይኑር አናውቅም። ምን ይሻላል? ለማንኛውም ፈጠን ፈጠን እያልን እንሂድ። ሳንርቅ መንደር ብናገኝ።
ኅሊና፦ አንድ ቦታ ቁጭ እንበልና የሚያልፍ ሰው እንጠብቅ። ውኃ አጠጡን ብንላቸው አይጨክኑብንም።
ጥበቡ፦ ብንመለስ አይሻልም? ጥለውን የሄዱትን ባንደርስባቸውም እንኳን ሌላ መኪና እናገኛለን።
ኅሊና፦ ከአሁን በኋላ የሚነሣ መኪናም የሚኖር አይመስለኝም። እኔ ደግሞ ዝያለሁ። ትንሽ ልረፍ።
ጥበቡ፦ ጎሽ! አየሽ እዚያጋ አንድ ገበሬ ይታየኛል። ወደ እርሱ ቀርበን ለምን አናነጋግረውም?
ኅሊና፦ ተመስገን፣ ይህም ታላቅ ጸጋ ነው። በል ወደ እርሱ እንገሥግሥ።
ገበሬው፦ በዚህ ጭር ባለ ስፍራ ምን ትሠራላችሁ?
ኅሊና፦ ሀገር ልንጎበኝ መጥተን፣ መንገድ ጠፋብን። ከኛ ጋር የነበሩት ሰዎችም ለጊዜው ተሰወሩብን። እኛ ስንጎበኝ ቀስ ብለን ስለነበረ ጥለውን ሄዱ።
ገበሬው፦ በሉ ወገኖች ኑና እህል ቅመሱ። እግዚአብሔር ይመስገን ከሚበላውም ከሚጠጣውም እንካፈላለን።
ጥበቡ፦ እግዚአብሔር ይስጥልን። ውኃ ከጠጣን ሳይመሽብን ብንሄድ ይሻላል።
ገበሬው፦ ሳይመሽብን አላችሁ?! የሚቀራችሁን መንገድ ባለማወቃችሁ ስለሆነ አይፈረድባችሁም። ገና መች ተነካና። ይልቁንም ነገ፣ ከማለዳ ጀምሮ የሚያልፉ አውቶቢሶች ስላሉ፣ እነሱን ብትጠብቁ ነው የሚሻለው። እዚህ ብታድሩ ነው የሚበጀው። እራት አብረን እንበላለን፤ ለመኝታም አታስቡ። ተመስገን! እንኳን መጣችሁልን! በረከት እኮ ነው ያመጣችሁልን! ለረጅም ጊዜ የጠበቅነው ዝናብ መጣ!
ጥበቡ፦ መቼም እንዳናስቸግር ፈርተን ነው እንጂ። ምክርዎን መስማትማ ይገባናል።
ኅሊና፦ እጅግ በጣም እናመሰግናለን። ለዚህ የሚቀርብ መንደር አለ እንዴ? ወይንስ ብቻችሁን ናችሁ?
ጥበቡ፦ ኧረ ገበሬው እየሰማን አይመስልም ኅሊና! ጭራሽ ወደ ውጭ ወጣ። ዝናቡ በላዩ ላይ እየወረደ እጆቹን ዘርግቶ ፈጣሪን የሚያመሰግን ይመስላል። ወደ ደጃፍ ተጠግተን እንመልከተው። በደንብ ሲመለከቱት መሬቱን የሚያነጋግር ይመስላል።
ኅሊና፦ ኖር፣
ገበሬው፦ ኧረ በጻድቃን!
ጥበቡ፦ ከመሬቱ ጋር እየተነጋገሩ ነበር እንዴ?
ገበሬው፦ ምድሪቱን እንኳን ደስ ያለሽ እያልኳት ነበር፤ እንዴት እንደረሰረሰች! ደርቃ ነበር እኮ።
ጥበቡ፦ ለመሆኑ ውኃ ከየት ነበር የምታገኙት?
ገበሬው፦ እስካሁን የሰበሰብነው ውኃ ከዓለት ከሚመነጭ ምንጭ ነበር። ልጃችን ነች እየቀዳች የምታመጣው። ማንበብና መጻፍም ትችላለት።
ኅሊና፦ እውነትም ተመስጣ እያነበበች ነው። ምን እያነበብሽ ነው የኔ ቆንጆ? ስምሽስ ማን ነው?
ልጅቷ፦ ስሜ የኔ ወርቅ ነው፣ የማነበው ደግሞ ወንጌልን ነው።
ኅሊና፦ የትኛውን ወንጌል?
የኔ ወርቅ፦ የዮሐንስ ነው! ለአባባና ለእማማ ሁሌ አነብላቸዋለሁ።
ጥበቡ፦ ሳቅና ፈገግታሽ ያምራል። ለመሆኑ የትኛውን ክፍል ነው እያነበብሽ ያለሽው?
የኔ ወርቅ፦ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራትን ነው፤ የሳምራዊቷን ታሪክ።
ኅሊና፦ ከታሪኩ የገባሽን ልታስረጅን ትችያለሽ?
የኔ ወርቅ፦ ኢየሱስ ጠማው። ሳምራዊቷ ሴት ደግሞ ውኃ ወዲያው አልሰጠችውም። እንዲያውም ውኃ ስጠኝ ትለዋለች። እኔ አነባለሁ እንጂ ምሥጢሩን የሚያስረዳኝ አባባ ነው።
ገበሬው፦ ጌታ እኮ “የሕያው ውኃ ምንጭ እንደሆነ” ተናግሮአል። ይኸው ልጃችንም ጀንበር ልትጠልቅ ስትል የሕይወትን ቃል ታነብልናለች። እኛ በሥራ ደክመን ወደ ቤታችን ስንገባ ኃይል የሚሰጠንን ቃል እንሰማለን። የተጠማችን ነፍስ የሚያረካ፣ አጥንትን የሚያለመልም፣ የደረቀ ሕይወትን የሚያረሰርስ የሕይወት ውኃ! ‘ማንም የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ’ ብሎ የለምን? ዝናቡ መሬቱን እንዳራሰው፣ የእግዚአብሔርም ቃል ያለ ፍሬ አይመለስም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *