ከሰማይ መናን አወረደላቸው

“ከሰማይ መናን አወረደላቸው…”

ኅሊናና ጥበቡ በመንገድ ላይ ናቸው። ከረጅም ጉዞ በኋላ ያሳፈራቸው አውቶቢስ ድንገት ችግር ገጠመው፤ ከሕዝቡ ጋር ወርደው ከመንገድ ዳር ባለው መስክ ላይ መመላለስ ጀመሩ።

ኅሊና፡ – ሣሩና ቅጠሉ፣ አበባውም እንዴት ያምራል! የመስከረምና የጥቅምት ውበት ለብቻው ነው። የክረምት ዝናብ ምድርን አጥግቦ፣ ለሰው ልጅ የምግብና የኑሮ፣ የውበትም ተስፋ ሲሆን እንዴት ደስ ይላል።

ጥበቡ፡ -ለመሆኑ ለመኖር የሚያስፈልጉን ነገሮች ምን ምን ናቸው ትያለሽ?

ኅሊና፡ -እንዳካባቢው እና እንደ ሰዉ የሚለያይ አይመስልህም?

ጥበቡ፡ – ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ የመሳሰሉት ላይ የምንስማማ ይመስለኛል።

ኅሊና፡ – ትክክል ብለሃል። ግን ከዚህ በተጨማሪ መና አያስፈልገውም ብለህ ነው? አለበለዚያ ረሃቡን ማን ይችለዋል?

ጥበቡ፡ – የምን ረሃብ?

ኅሊና፡ – የምግብ  ረሃብ ማለቴ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ቃል ረሃብ ማለቴ ነው።

ጥበቡ፡ – እንዴት አይነት ረሃብ ነው?

ኅሊና፡ – እንዴ! “የሰው ልጅ በምግብ ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር በሚወጣውም ቃል ነው የሚኖረው”ተብሎ ተጽፎ የለምን?

ጥበቡ፡ -ግን…መና ስትዪ አልገባኝም።

ኅሊና፡ – ያልተጠበቀ የሰማይ ስጦታ ነዋ!

ጥበቡ፡ – ለእስራኤል ሕዝብ እንደወረደው ዓይነት ማለትሽ ነው? ሲጀመር ሰው ሁሉ በረሃን ያቋርጣል ማለት መቼም ያስቸግራል። በበረሃ ለማያልፍ ሰው መና ምን ያደርግለታል?

ኅሊና፡ – መናማ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።

ጥበቡ፡ – ያልራበው ሰው አሁን ምን መና ያስፈልገዋል?

ኅሊና፡ – እኔ እንደሚመስለኝ፣ ረሃብና ረሃብ አለ እንዳልኩህ ሁሉ፣ እንዲሁም መናና መናም አለ።

ጥበቡ፡ -ምን ማለትሽ ነው?

ኅሊና፡ -ለቁመተ ሥጋ የሚያስፈልግ መና አለ፤ ለመንፈሳዊ ሕይወት የሚያስፈልግ መና ደግሞ አለ። ሕዝበ እስራኤል በረሃውን ያቋረጠው የምድርን ፍሬ እየበላ ሳይሆን ከላይ የወረደ መናም እየተመገበ ነበር፤ አየህ፣ መናን ያገኘ ሕዝብ በረሃን ማቋረጥ ቻለ፤ ሆኖም ቁሳዊውን ነገር ብቻ መብላት አይበቃቸውም ነበር። ደምናው፣ ቃሉ፣ የእግዚአብሔር መሪነትና ጥበቃ፣ ምክርና ተስፋ ባይኖር ኖሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር ባልገቡ ነበር። ወደ ግብ ለመድረስ ተስፋ በጣም ያስፈልጋል። በእግዚአብሔር ቃል የሚጽናናና ተስፋ የሚያገኝ ሕዝብም የሕይወትን ውጣ ውረድ ይወጣዋል።

ጥበቡ፣ “መና”ን የእግዚአብሔርን ቃል ምሳሌ መሆን ይችላላ ማለት ነው።

ኅሊና፡ – በሚገባ! በዚህ ምድር ላይ፣ ወሳኙና ብርቅዬው መና የእግዚአብሔር ቃል ነው። እንዲሁም “በበረሃ የነበረው ሕዝብ ለመጀመርያ ጊዜ መናን ሲያይ፤ ይህ ምንድነው? ብሎ ጠየቀ። መና፣ መጠየቅን፣ መመርመርን፣ ለመማር መፈለግን ያመለክታል።

ጥበቡ፡ – ታዲያ የእግዚአብሔርም ቃል መጠየቅን፣ መመርመርን፣ ለመማር መፈለግን፣ ትሕትናን ያሻል ማለትሽ ነው?

ኅሊና፡ – አዎን፤ ጥሩ ብለሃል። በተጨማሪም፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ በበረሃ መናን ሲመገብ፣ መናውም የተለያየ ጣዕም ነበረው። አንዳንዴ የአትክልት ጣዕም፤ አንዳንዴ ደግሞ እንደ ማር ይጣፍጥ ነበር። በሌላ በኩል የሰውን ሕይወት በጉዞ ስንመስለው፣ ጉዞ አቅጣጫና ግብ አለው፤ አለበለዚያማ ጉዞ ሳይሆን ዙረት መሆኑ ነው።

ጥበቡ፡ – የሕይወት ጐዳና ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለው ምንም አያጠራጥርም።

ኅሊና፡ – የበረሃ ጉዞ ደግሞ ብዙ አደጋ አለው፤ ምግብ ወይንም ውሃ ሲጎድል የሞት አደጋ ላይ መውደቅ ይቻላል። የእግዚአብሔር ሕዝብም በበረሃ ነው ከአምላኩ ጋር የተዋወቀው። እግዚአብሔርና ሕዝቡ ኪዳን ያቆሙት በበረሃ ነው። ሕዝቡም ከበረሃ ጉዞ በኋላ ነው ወደ ተስፋ ምድር የገባው። ሙሴም በበረሃ በሚገኘው በሲና ተራራ ላይ ነው የሕግ ጽላትን የተቀበለው። ሕጻኑ ኢየሱስም ከቅድስት ማርያምና ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር በረሃን አቋርጧል። ክርስቶስም ዘወትር ወደ በረሃማ ቦታ እየሄደ ይጸልይ እንደነበርም ወንጌል ይገልጻል።

ጥበቡ፡ – ትልልቅ ተግባራት በበረሃ ከተከናወኑ እግዚአብሔርን ለማግኘት ወደ በረሃ መሄድ ሊያስፈልግ ነዋ?

ኅሊና፡ -በረሃ ሲባል ቁሳዊ በረሃ ማለት ብቻ አይደለም። በረሃ እኛ ለብቻችን፣ ከነድክመታችን፣ በትንሽነታችን፣ ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበት ሁኔታ ነው። በዚያ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን፣ የምንጸልይበት ማንኛውም ቦታ፣ መናፈሻም ሆነ መኖርያ ቤታችን፣ ሸለቆም ሆነ ተራራ፣ ገጠርም ሆነ ከተማ በረሃችን ሊሆን ይችላል። ብዙ ሕዝብ ባለበትም ቦታ ሳይቀር በበረሃ መሆን እንችላለን።ቁም ነገሩ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት መመቻቸታችን ነው። ጨለማው በረሃ ሲሆን የእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ይሆንልናል። የሕይወት ውጣ ውረድ በሐዘን በረሃ ውስጥ ሲጨምረን፣ የእግዚአብሔር ቃል የመጽናናት መና ሆኖ ያወጣናል። በቁጣ በረሃ ውስጥ ስንገኝ፣ የእግዚአብሔር ቃል የሰላም መና ሆኖ ያረጋጋናል። በሕመም ስቃይ ውስጥ ስንሆን፣ የእግዚአብሔር ቃል የሚያድን መና ሆኖ ይፈውሰናል። ትልቁ ቁም ነገር፣ አመጋገባችን ላይ ነው። የቃልህ ምሥጢር ምንድነው እያሉ፣ በትሕትና መጠየቅ ያሻል። ያኔ መናው ይጣፍጠናል። ሕይወታችንንም ያጣፍጠዋል።

ጥበቡ፡ -“ቃልህን ተመገብሁ” የሚለው የነቢዩ ኤርምያስ ቃል ትዝ አለኝ።

አውቶቢሱ ከተጠገነ በኋላ፣ ሹፌሩ ጥሩምባ መንፋት ጀመረ፤ ሰዎችም እየተቻኮሉ ወደ አውቶቢሱ ሲገቡ፣ ጥበቡና ኅሊናም አንዳንድ ሰዎችን ተከትለው ወደ ተሽከርካሪው አመሩ። ከመግባታቸው በፊት ግን ወደ ኋላ መለስ ብለው በፈገግታመስኩን ቃኙት። ቁም ነገር የተወያዩበትን መስክ መሰናበት የፈለጉ ይመስል። ጉዞአቸውንም ቀጠሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *