ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የ2010 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለምዕመናን ለመላው የአገራችን ህዝቦች ያስተላለፉት መልዕክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ  የኢትዮጵያ  ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የ፳፻ (የ2010) ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለምዕመናንና     ለመላው  የአገራችን ህዝቦች ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ለሰው ሁሉ ወንጌልን አስተምሩ፡፡” (ማር.16፡15)

ብፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና፤ ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ምዕመናንና የአገራችን ህዝቦች በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና  በራሴ ስም እንኳን ለ2010 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም  ምኞቴን ላስተላልፍላችሁ እወዳለሁ፡፡ እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ በሰላም አሸጋገራችሁ፡፡

   “ የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ፤ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ፡፡” (መዝ 64፡11)

   ዛሬ ሁላችንም በሕይወት እንኖርበት ዘንድ እግዚአብሔር ስለሰጠን አዲስ ዓመት የምናመሰግንበት ነው፡፡ አዲሱ አመት ያለፈውን ጉዟችንን ለማየትና በውስጣችን ያለውን ደካማነት በማስወገድ ሕይወታችንን እንድንመራ ኃይል ይሆነናል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ዓመታትን በየዘመኑ ሲሰጠን ፍሬ እንድናፈራበት ነው፡፡ ይህውም መልካም ሰዎችና ትሁት፣ በባህሪያችን ደጎችና በሥራችን ጠንካሮች በመሆን ዓመቱ የጽድቅና የበረከት እንዲሆንልን ተስፋ በማድረግ ልንጀምረው ይገባል፡፡

አዲሱ ዓመት የሚሰጠን የሥጋና የመንፈስ ደስታ አለው፡፡ በመሆኑም ከአሮጌው ዓመት ተለይተን አዲሱን ስንጀምር ብዙ ራዕዮች፣ ተስፋዎችና፣ ዕቅዶች ይዘን በመሆኑ ሁላችንም የምንደሰትበት በበለጠም ከእግዚአብሔር አምላካችን ጋር በመሆን እርሱ ያስተማረንንና የሚፈልግብንን በተግባር የምንፈጽምበት ነው፡፡

“ ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት መዝ 150፡8

እግዚአብሔር በሰጠን ዓመት በውስጡ በያዛቸው ቀናቶች በመንፈሳዊነት ታግዘን ወደ ታላቅ እድገትና ደረጃ ለመድረስና ውጤታማ ለመሆን መልካም ነገሮችን በመስራት የተባረኩና የተቀደሱ ቀናቶች በማድረግ ልንጠቀምባቸው ያስፈልገናል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተ ድርቅ እነደነበረ ይታወቃል፡፡ ይህን በማስታወስ በአዲሱ ዓመታችን እግዚአብሔር በምሕረቱና በቸርነቱ ጎብኝቶን ለመላው አገራችን የተስተካከለ የወቅቶች ስጦታውን በመስጠት ህዝቦቹ፤ እንስሳቶቹና አራዊቱ በልተውና ጠጥተው በእርሱ  ቸርነት የሚገኘው መከር እንዲበዛልንና ጥጋብ ሆኖ ሁሉም በደስታ እንዲኖሩ ያደርግልን ዘንድ ጸሎታችንና ምኞታችን ነው፡፡

ዝናብን በማዝነም ምድርን ትጎበኛለህ ፍሬያማ በማድረግ ታበለጽጋለህ ምንጮችን በውሃ ትሞላለህ ለምድርም ሰብልን ትሰጣለህመዝ 65፡9

በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርና የእምነት ሰዎች በመሆን ሃይማኖታዊ ትዕዛዞችንና ሥነ ምግባሮችን በመጠበቅ አላስፈላጊ ከሆኑ የሥነ ምግባር መበላሸትን  ከሚያመጡ ጎጂ ባህሎችና መጥፎ ሱሶች ቤተሰባችንን፣ ልጆቻችንንና ማኅበረሰባችን በመጠበቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባርን በማስተማር ጥሩ ዜጎች ይሆኑ ዘንድ አደራ ማለት እንወዳለን፡፡

መገናኛ ብዙኃንም መልካም ዜጎችን ከመፍጠር አንጻር ገንቢና አስተማሪ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ትውልዱን መታደግ እንደሚኖርባችሁ መግለጽ እንፈልጋለን፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን

በደስታ የተቀበልነውን ርዕሰ ዐውደ ዓመት ስናከብር አስታዋሽና እረዳት ለሌላቸው ችግረኛ ወገኖች፣ ህሙማን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ አቅመ ደካሞች በፍቅርና በደስታ መንፈስ በመርዳትና አብረን በማሳለፍ ልባቻንን መንፈሳዊ እርካታ በማጥገብ በዓሉን በደስታ እናሳልፍ ዘንድ አደራ እላለሁ፡፡

በ2010 ዓ.ም በአገራችን የሚደረገው 19ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባዔ በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ሕያው ብዝሃነት፣ ሰብዓዊ ክብርና፣ ሰላማዊ አንድነት ለምሥራቅ አፍሪካ አገራት በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደው ጉባዔ “እግዚአብሔር በነገሮቻችን ሁሉ ይከብር ዘንድ” (1ጴጥ 4፡11) መላው ምእመናን ለጉባዔው መሳካት ይጸልዩና የሚቻላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ መንግስትና መላው ህዝባችንም ለአገራችን ታላቅ ክብር የሆነውን ጉባዔ በእንግዳ ተቀባዮች የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለማካሄድ ተገቢውን ትብብር ያደርጉልን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

በተለይ በዚህ በአዲሱ ዓመት ለሕጻናትና ለወጣቶች መልእክት አለኝ፡፡ መስከረም ወር ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ስለሆነ በአዲስ ተስፋና በጽኑ ዓላማ ትምህርት  ቤት ገብታችሁ ትምህርታችሁን በርትታችሁ ተማሩ፡፡ እግዚአብሔር ሕፃናትንና ወጣቶችን ይወዳል፡፡ እናንተም ውደዱት፡፡ ወላጆቻችሁንና መምህራኖቻችሁን አክብሩ፡፡ ይህን ካደረጋችሁ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁና ለአገራችሁ ኩራት ትሆናላችሁ፡፡

ሰላም የሁላችን ጸጋ፤ የኅብረታችን ማሰሪያ፤ የሀገራችን የልማትና የብልጽግና መሠረት ነውና የሰላሙ ንጉሥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሙን ይስጠን፡፡

በመጨረሻም በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን፣ በህመም ደዌ የተያዛችህ ህሙማን ሁላችሁ እግዚአብሔር ምህረቱን እንዲሰጣችሁ፣ በየማረሚያ ቤቶች የምትገኙ የህግ ታራሚዎች ከእስራት እንዲፈታችሁ በመመኘት፣ የአገርን ድንበርና ፀጥታ የምታስከብሩ የፀጥታ ሃይሎች፣ ከአገር ውጭ ሰላም ለማስከበር የተሠማራችሁ፣ በስደት ላይ ያላችሁ ሁላችሁ እንኳን ለ2010 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ፡፡

አዲሱን ዓመት እግዚአብሔር አባት ባርኮልን፣ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የትዕግስትና የመቻቻል ዓመት ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገራችንንና ህዝባችንን ይባርክ!!

†ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ/ም

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *