የጾመ ፍልሰታ መልዕክት

የጾመ ፍልሰታ መልዕክት
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2009 ዓ. ም. የጾመ ፍልሰታን በማስመልከት ለመላው ካቶሊካውያንና በጐ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ ያስተላለፉት መልዕክት

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ካቶሊካውያን ምዕመናን እንኳን ለ2009 ዓ. ም. ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ በማለት ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ እስከ 15 ቀን ድረስ ምዕመናን የእመቤታችንን በረከት ለማግኘት በጾም፣ በጸሎት፣ በምህላና፣ በሱባኤ በማሳለፍ የአምላክ አንድያ ልጅ እናት እና የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ለሆነችው እመቤታችን ማርያም ምሥጋና ያቀርቡላታል፡፡
ዘመነ ፍልሰታን እናቶቻችንና አባቶቻችን በእመቤታችን በመተማመን በታላቅ መንፈሳዊነት ይጾሙት እንደበረ አሁንም ወጣቶችና ታዳጊዎችም ከዓለማዊ ነገሮች በመራቅ በበለጠ መንፈሳዊነት በጾምና በጸሎት ያሳልፉታል ወንጌላዊው ዮሐንስ ማርያምን በቤቱ እንደተቀበላት ሁሉ እኛም እመቤታችንን በልባችን ውስጥ ልንቀበላት ይገባል (ዮሐ 19፡27)፡፡
የደኅንነታችንን ሥራ በመፈጸም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ከተመለሰ በኋላ የሁላችን ተወካይ የሆነችው ብፅዕት ድንግል ማርያም ልጇን ተከትላ በነፍስና በሥጋዋ ወደ ሰማይ ወጥታለች፣ በቅድስት ሥላሴ ፊት ደግሞ ባልደረባ እንድትሆን ተመርጣለች ጌታችንም የእረፍት ቦታ ሆኗታል፡፡ “ይህቺ ለዘለዓለም ማረፊያ ናት” (መዝ 132፡14)፡፡
የተወደዳችሁ ምዕመናን በዚህ የጾመ ፍልሰታ ጊዜ ሁላችሁም ከፍሬ አልባ ነገር ተጠብቃችሁ ህሊናችሁን በመመርመር በመንፈሣዊነት ለመበርታትና ለመጠንከር በፍፁም ደስታ መንፈሣዊውን ጾም በመጾም ከዚህም ጐን ለጐን ችግረኞችን በመርዳት፣ በማብላትና በማልበስ የተለያዩ የበጐ ሥራ አገልግሎቶችን በመፈጸም የቅድስናን ፍሬ የምታፈሩበት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡
ወላዲት አምላክ ሁሌም ትወደስ
በእመቤታችን ጾም አማካይነት እግዚአብሔር አምላካችን እኛንና አገራችንን ይባርክ

 ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት
የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኀብረት ሊቀመንበር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *