የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለመላው የአገራችን ምዕመናን የ፳፻፱ (የ2009) ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ  ለመላው የአገራችን ምዕመናን የ፳፻፱ (የ2009) ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

 ‹‹ እግዚአብሔር ዓለምን እንዲሁ ስለወደደ አንድ ልጁን ሰጠ ስለዚህ በልጁ የሚያምን           

ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም ›› (ዩሐ 3፡16)

ብፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና፤ ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

     ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ካቶሊካውያን ምዕመናንና የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2009 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ፤ በማለት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴም ስም መልካም በዓል ይሁንልን አያልኩ የመልካም ስጦታ ሁሉ ሰጪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በዓላችንን የተቀደሰና የተባረከ ያደርግልን ዘንድ ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡

ጌታችን  የኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ዓለምን ለማዳንና የሰው ልጆችን ከሰይጣን ባርነት ነፃ ለማውጣትና የሰማይን በር ለመክፈት ነው፡፡ ‹‹የሁሉ ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ወደ ምድር መምጣቱና ሁሉ በእርሱ የሆነው ከመጀመሪያ የነበረው ያ ቃል ሥጋ ሆነ ›› (ዩሐ 1፡ 1-3) ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር አባታችን አዳኛችን የሆነውን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰዎችን ሁሉ ለማዳን በሰጠን የዘለዓለም ሕይወትን እንድናገኝና በማያልቀው ሕይወት እውነተኛና ዘላቂ መዳኛችንን ይዘን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ነው፡፡ ይህም በሙሉ ልባችን እርሱን ማፍቀር አብነቱን መከተል ይጠይቃል፡፡

እግዚአብሔር በፀጋውና ወሰን በሌለው ታላቅ ፍቅር አንድ ልጁን ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስን እኛ ህዝቦቹን ለማዳን የላከበትን የልደቱን ቀን በየዓመቱ ስናከብር በታላቅ ደስታ ነው፡፡ ምክንያቱም የዓለም ሁሉ ብርሃንና ከፍቅር ሆኖ ስለመጣልን ነው፡፡ሁላችንም ምዕመናን ከእውነተኛ ደስታ የተነሣ ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት ይገባል የልደት በዓል የእግዚአብሔር ስጦታ ማመስገኛ ጊዜያችን ነው፡፡ ይህውም የእግዚአብሔር ክብር ያየንበት ስለሆነ ነው፡፡

የጌታችን ልደት ሰውና አምላክ የተቀራረቡበት፣ ከአምላክ ጋር የተሣሠሩበት ሰው ከአሮጌው ሕይወት ወደ አዲሱ ሕይወት ፣ ከኃጢያት ወደ መልካምነት፣ ከውርደት ወደ ክብር የቀረብንበት ነው፡፡ በመሆኑም ከዓለም ጨለማ ወጥተን እሱን ከሙሉ ልባችን በመከተል በብርሃን መኖር ይገባናል፡፡ ለዚህም ጌታችን በቃሉ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይኖረዋል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› ይለናል (ዩሐ 8 ፡12)

እግዚአብሔር አንድ ልጁን በመላክ እኛ ሰዎች የሕይወቱ ተካፋይና ልጆቹ እንድንሆን በዚህም የእርሱ ቤተሰብ ሊያደርገን ነው፡፡ እኛም በኑሮኦችን ውስጥ የሕይወት ጌታ የሆነውን መሢሁን መመልከትና ወደ ሕይወት በሚያደርስ መንገድ ከእርሱ ጋር በመጓዝ ሁልጊዜ በዘለዓለማዊነቱ ጥላ ሥር መኖር አለብን፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን

የክርስትና ሕይወታችን ሁልጊዜ ከጌታ ጋር በህብረት መኖር አለበት፡፡ እሱ ለእኛ ለሰው ልጆች እንድንካፈል ከሰጠን ትልቅ ነገር ፍቅር ነው፡፡ እርሱ ሁላችንንም እኩል እንደሚወደን እኛም በአርዓያ እግዚአብሔር ለተፈጠሩ ለሰው ልጆች ሁሉ ጥልቅ የሆነ ፍቅር፤ የመግባባትና የመቻቻል ብሎም የመቀራረብ መንፈስ በየዕለታዊ ኑሮአችን መግለጽና ማሳየት ይኖርብናል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የየዕለቱ ሥራችንን በታማኝነት ማከናወንና የእርሱን መንገድ ይዘን መጓዝ ይኖርብናል፡፡ የሕይወት ደስታ የምናገኘው በእርሱ ነውና፡፡

“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወለዶላችኋል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡” (ሉቃስ 2፡11)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሐም በበረት ውስጥ መወለዱን ስናከብር እናቶችንና ሕፃናትን በማስታወስ ሊሆን ይገባል፡፡ የወለዱ እናቶችን እንኳን ማርያም ማረቻችሁ በማለትና የተወለዱትንም ሕፃናት እነኳን ተወለዳችሁ አንኳንም በሰላም ወደዚች ምድር መጣችሁ በማለት ልንቀበላቸውና ልንከባከባቸው ይገባል፡፡ የሕፃናት መብት ይከበር፡፡ ከሁሉ በላይ ሕፃናት የሚሹት ፍቅርን ነውና እናፍቅራቸው፡፡ የልደት በዓል የቤተሰብ በዓል ነውና “ኢየሱስ ፡ ማርያም ፡ ዮሴፍ ፡ ቤተሰቦቻችንን ባርኩልን ብለን እንጸልይ፡፡”

ጌታችን ድሆችን መርዳት እንዳስተማረን እኛም ይህን  የጌታችንን የመዳኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ስናከብር በታላቅ ልግስና ድሆችንና ችግር ላይ የሚገኙትን ሕፃናትን በመርዳትና ካለን በማካፈል፤ አንዲሁም በዓሉንም ከእነሱ ጋር በማሳለፍ ለእነርሱ በመራራትና የአቅማችንን ሁሉ በደግነት በመለገስ እንድናሳልፍ ላስገነዝባችሁ እወዳለሁ፡፡ እግዚአብሔር ሁሌም ከሰጠነው በላይ አብዝቶ ይሰጠናልና፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን

በአሁኑ ጊዜ መንግስት ኢትዮጵያ ሀገራችንን በበቂና በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር  በተያያዘው የተሐድሶ ጉዞ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን በማየት ላይ እንገኛለን ይህንንም ማስፈጸም እንዲችሉ ለተለያዩ ሃላፊነቶች የተመረጡ ሰዎች እንደተመደቡ  ይታወቃል፡፡ በእኛ እምነት የእነርሱ ለዚህ ታላቅ ሃላፊነት መመረጥ በክብር ከፍ ለማለት ሳይሆን የህዝቦችን ጥያቄዎችን በተገቢው ሁኔታ መልስ ለመስጠትና ለማስተዳደር መሆኑ እናምናለን፡፡ ስለሆነም ሁላችንም በመልካም አስተዳደር ፍትሐዊ የሆነ ሥራዎችንና ውጤቶችን እንደምንጠብቀውና እንደምንመኘው ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንደሚሠሩና እንደሚያስፈጽሙ ታላቅ እምነት አለን፡፡

በማያያዝም መንግስት አሁን ወደታች በመውረድ የህብረተሰቡን ችግሮች ለማስተካከልና ለመቅረፍ በሚያደርገው ውይይት ሰምቶ ዝም ብሎ ማለፍ ከሆነ አመርቂ ውጤት ሊገኝ  ስለማይችል በቁርጠኝነት የተነሳበትን ዓላማና ለህዝቡ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም በመተማመን ነው፡፡

“በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በማድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን፡፡” (ሉቃስ 2፤14)

 የሰላሙ ንጉሥ ሰላሙን ለምንወዳት ለአገራችን ለኢትዮጵያና ለሁላችን እንዲሰጠን እንጸልይ ፡፡

      በመጨረሻም በዚህ የጌታችን የልደት በዓል በተለያዩ ሕመሞች የታመማችሁትን  በሙሉ እግዚአብሔር እንዲምራችሁ፣ በየማረሚያ ቤቶች የምትገኙ የህግ ታራሚዎች ከእሥራት እንዲፈታችሁ፣ በተለያዩ ሥራዎች በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በአገር ውስጥ  የአገር ድንበርና ፀጥታ ለማስከበርና በሌሎች አገሮች የሰላም ተልዕኮ በመስጠት ላይ የምትገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላቶች በሙሉ እንኳን ለ2009 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን ለመላው የክርስትና አማኝ ወገኖች አስተላልፋለሁ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !

…ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት

የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ሊቀመንበር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *