ፕሬስ ሪሊዝ

ፕሬስ ሪሊዝ

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅት ላይ ነች

የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት በማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ ባካሄደዉ በ18ኛዉ ጉባኤ ህብረቱን ለ4 ዓመታት ኢትዮጵያ በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዉያን  የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት አማካኝነት በሊቀመንበርነት እንድትመራና በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. የሚካሄደዉን 19ኛዉ ጉባኤ እንድታስተናግድ መርጧታል፡፡ ህብረቱ አመሰያ (AMECEA) በሚለዉ ምህፃረ ቃል በሰፊዉ የሚታወቅ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማላዊና ዛምቢያ አባል ሃገራት ናቸዉ፤ በተጨማሪም ጅቡቲና ሶማሊያ የህብረቱ ተባባሪ አባል ሃገራት ናቸዉ፡፡

ኢትዮጵያ ህብረቱ ከተቋቋመ ጀምሮ አባል የነበረች ሲሆን ጉባኤዎቹን የማስተናገድ እድሉን አግኝታ አታዉቅም፤ በስብሰባዉ ከ300 በላይ የሚሆኑ የካቶሊክ ጳጳሳት፣ የቅድስት መንበር ቫቲካን ተወካዮች፣ የቤተክርስቲያን መሪዎች፣ በሃገራቸዉ ልዩ ልዩ ሃላፊነት ላይ የተሰማሩና አገራቸዉን ወክለዉ የሚሳተፉ ምእመናን፣ የአጋር ድርጅቶች ዳይሬክተሮች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ጉባኤዉ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ያገኛል፡፡

ይህ በምስራቅ አፍሪካ ለምትገኘዉ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታላቅ ጉባኤ ሲሆን የአገራችንንም መልካም ገፅታ ይበልጥ ለማስተዋወቅ የሚረዳ ታላቅ አጋጣሚ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ እንድታስተናግድ ስትመረጥ ከፍተኛ የቤተክርስቲያን መሪዎችና የዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች አገራችን ያላትን የረጅም ዓመታት ታሪክና መስህቦችን ለማወቅ ካላቸዉ ጉጉት እንዲሁም አገራችን ያለችበትን የእድገት ደረጃ ለማየት ካላቸዉ ፍላጎት የተነሳ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነዉ፡፡ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ያላትን የሰላምና የመከባበር ባህል ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር ለመካፈል የምትጠቀምበት አጋጣሚ መሆኑን ተገንዝባ የአስተናጋጅ ሃላፊነቱን ተቀብላለች፡፡ ቤተክርስቲያን ይህን የተቀበለችዉን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣትም ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገች ነዉ፡፡

ይህንንም በ2010 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ላይ የሚካሄደው ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ሁለገብ ዝግጅት በተሟላ  ሁኔታ መጀመሩን ቅዳሜ ታህሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ይታወጃል፡፡ በዚሁ እለት የጉባኤዉ መሪ ቃልና አርማ የሚቀርብ ሲሆን ለዚሁ ጉባኤ መሳካት የተዘጋጀዉ ፀሎትም በመላዉ ምስራቅ አፍሪካ እለት በእለት እንዲጸለይበት ይሰራጫል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ የሁሉም ምእመናን፣ የካቶሊክ ተቋማትና ተባባሪዎች፣ እንዲሁም በጎ ፍቃድ ያለቸዉ ሁሉ በዝግጅቱ የሚሳተፉበትን አቅጣጫ ላይ ዉይይት ይደረጋል፡፡

 

የዚህ ጉባኤ የመጨረሻ ዉጤት የሚሆነዉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአፍሪካ ዉስጥ ያላትን የሐዋሪያዊና የማህበራዊ ልማት አስተዋፅኦ ይበልጥ አጠናክራ ለሰዉ ልጆች ሁለንተናዊ እድገት በምን መልኩ መስራት እንዳለባት ለቀጣይ 4 ዓመታት አቅጣጫ የምትይዝበት ሲሆን፤ ቤተክርስቲያን ለሰላም፣ ለፍቅርና ለእድገት እንዲሁም ለመልካም የቤተሰብ ሕይወት መገንባት ካለንበት አስቸጋሪ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ያላትን ማህበራዊ ሃላፊነት ምን እንደሚመስል በመዳሰስ የትግበራ አቅጣጫ ትይዘለች፡፡ ቤተክርስቲያን በመላዉ ዓለም ለሰዉ ልጅ ሁሉ ያለምንም አድሎ እንደማገልገሏ መጠን በምስራቅ አፍሪካም የምታደርጋቸዉ ሐዋሪያዊና ማህበራዊ አገልግሎቷ ለሁሉም ሰው ማለትም ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቀለም ሳይለይ ይደርሳሉ፡፡  19ኛዉ የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረትም በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ህዝቦች በቀጣዮቹ 4 ዓመታት ለምታበረክተዉ አገልግሎት ወሳኝ ጉባኤ ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም 19ኛዉ የህብረቱን ጉባኤ ለማስተናገድ ስትዘጋጅ የመላዉ ኢትዮጵያዉያንና በጎ ፍቃድ ያላቸዉን ወገኖች ትብብር እንዳይለያት ትጠይቃለች፡፡ ከታህሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. የ19ኛዉ ጉባኤ ዝግጅት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሁሉም ሀገረስብከቶች በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚገኘዉ የህብረቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ በይፋ ይጀምራል፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *