በመንፈስ ቅዱስ አገልጋይ እህቶች ማህበር የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ እህት ቃለ መሃላ ፈጸሙ

በመንፈስ ቅዱስ አገልጋይ እህቶች ማህበር የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ እህት ቃለ መሃላ ፈጸሙ

እህት መሠረት ወልደማርያም የመጀመሪያዋ የመንፈስ ቅዱስ እህቶች ማህበር ኢትዮጵያዊት አባል በመሆን በድህነት ለማገልገል ቃለ መሃላቸዉን ፈጸሙ፡፡  ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ. ም. በመላው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በታላቅ መንፈሳውነት በሚከበረው ያለ አዳም ኃጢያት በተፀነሰችው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  ክብረ በዓል ዕለት ሥርዓቱ ተካሄዶዋል፡፡  ኮተቤ በሚገኘው የማህበሩ ዋና ቤት የቃል ኪዳን መሃላ የተደረገ ሲሆን ቅዳሴ ከመደረጉ በፊት በኢትዮጵያ የሚያገለግሉ የማህበሩ አባላት በተገኙበት በመስቀልና በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ምስል ፊት በመቆም ለእህት መሠረት ወልደማርያም  መልካም የአገልግሎት ሕይወት  እንዲሆንላቸው ተመኝተውላቸዋል፡፡

እህት መሠረት ወልደማርያም የመጀመሪያዋ የመንፈስ ቅዱስ እህቶች ማህበር
እህት መሠረት ወልደማርያም የመጀመሪያዋ የመንፈስ ቅዱስ እህቶች ማህበር

በመስቀል በመመራት ወደ ቤተ ጸሎት ከተገባ በኋላ በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት  ከወንጌል በኋላ እህት  መሠረት በቅዱስ ቁርባን ፊት በመቆም ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ ለመስጠት  እንዲሁም በማህበሩ ዓላማ ደንብ ለመገዛት  የመጀመሪያ መሃላ በመግባት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

የማሃበሩ አለቃ ሲስተር ሜሪ ስቴላ መሃላቸውን በመቀበል “የማህበሩ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ በማግኘታችን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን” በማለት የማህበሩን ዓርማ መስቀልና  የማሀበሩ መተዳዳሪያ ደንብ በመስጠት እህት መሠረት ወልደማርያም  የማህበሩ ሙሉ አባል መሆናቸውን አብስረዋል፡፡  በዚሁ ጊዜ በቦታው የተገኙት ሁሉ ደስታቸውን በዝማሬ ሲገልጹ የማህበሩ አባላት እህቶች እንኳን ደስ ያለዎት በማለት እህታዊ ሰላምታ አቅርበውላቸዋል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ አገልጋይ ደናግላን ማህበር 1977 ዓ. ም. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት  በመቂ ሀገረስብከት በዓለም ጤና፣ በወራጉ፣ በጮሌ፣ በሶዶ ሀገረስብከት በበዴሳ አካባቢ በጤና፣ በመዋለ ሕፀናት ትምህርት፣ በሴቶች ዕድገት ሥራ ፣በገጠር ልማት፣ በወጣቶች ሐዋርያዊ ህንፀት ዘርፍ ተሰማርተው አገልግሎት  እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የእህት መሠረት ወ/ማርያም ቤተሰብ የተገኙ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴውን የመሩት ከኬኒያ የመጡ በአገራችን ማህበሩ ያልገባ የመንፈስ ቅዱስ አገልጋይ አባቶች ማህበር አባል አባ ዮሴፍ  እንዲሁም  ከሆሳና ሀገረ ስብከት የጃጁራ ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቁምስና ቆሞስ አባ ዘመዴ አሸቦና አባ ታምራት   ስዩም ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *