ካቶሊካውያንን በአንድነት የሚያሰተሳስረው የክርስቶስ ንጉስ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ካቶሊካውያንን  በአንድነት  የሚያሰተሳስረው የክርስቶስ  ንጉስ  በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

በመላው ካቶሊካውያን ምዕመናን ዘንድ ከሚከበሩትና ምዕመናንን በአንድነት  ከሚያሰባስቡ   አንዱ የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ነው፡፡

_dsc0013

 

በሀገራችን ይህ በዓል ቤተክርስቲያን ከተመሰረተች ጀምሮ በደማቅ መንፈሳዊነት በሁሉ ሀገረስብት እየተከበረ ሲገኝ በዕለቱ የተለያዩ መርሃግብሮች ተዘጋጀተው አብዛኛው ምዕመናን አንድ ቀን ሙሉ ለቤተክርስቲያን ጊዜውን በመስጠት እርስ በርስ በመተዋወቅና በደስታ የሚያሳልፍበት ጊዜ ነው፡፡  ባለፈው  ዓመት በኀዳር 2008 ዓ.ም  በብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ  በመካከለኛው አፍሪቃ በባንገዊ ከተማ በይፋ የተከፈተው ልዩ የምህርት ዓመት ኢዮቬልዩ  ኀዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም በመላው ሀገረስብከቶች በይፋ የተዘጋበት ነበር፡፡

_dsc0039

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከኀዳር 24-25 2009 ዓ. ም. በብፁዕ  ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በዋዜማው በጸሎተ ቡራኬ የተጀመረው በዓል ስለ ምህረትና ንስሐ አስተምሮ፣ በእናቶችና በአባቶች፣ በገዳማውያንና በወጣቶች፣ በሕፃናት የእግዚአብሔርን ምህርትን የሚገልጹ ዝማሬ ሲቀርብ  የቅዱስ ቁርባን ስግደት፣ የፀጥታና የንስሐ ጊዜም ተከናውኗል፡፡ በመጨረሻም በቅዱስ ቁርባን ቡራኬ  የዋዜማው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

በበዓሉ ዕለት ከአዲስ አበባ ቁምስናዎችና ከከተማ ውጪ የሚገኙ ቁምስናዎች የመጡ ምዕመናንና ገዳማውያን  ከንጋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በልደተማርያም ካቶሊክ ካቴድራል በመገኘት  ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ከመላው የሰበካው ቆሞሳት ጋር በመሆን  በመሩት ሥርዓተ ቅዳሴ ሥርዓቱን ተከናውኗል፡፡

ብፁዕነታቸው ባቀረቡት ቃለ ምዕዳን “ክርቶስና ምህረት፤ ምህረትና ክርስቶስ የማይነጣጠሉ ናቸዉ” በማለት የክርስቶስን መሃሪነት ገልፀዋል፡፡  “ቤተክርስቲያን ያወጀችውን ልዩ የምህረት ዓመት ኢዮቬልዩ  ስናጠናቅቅ በክርስትናችን ጉዞ ላይ ለምህረት ትኩት በማድረግ እራሳችንን ከእግዚአብሔር ምህረት  ጸጋ ተካፋይ እናድርግ” በማለት ተማጥነዋል፡፡

ዓመቱን ሙሉ  በምህረት መሪ ቃል በመመራት የተለያዩ መንፈሳዊ አስተምሮ የተደረገ ቢሆንም  ሰባቱ መንፈሳዊ የምህረት ሥራዎችና ሰባቱ አካላዊ የምህርት ሥራዎች  በቀጣይነት የምንፈጽማቸው   ክርስቲያናዊ  የውዴታ ግዴታችን እንደሆኑም  ገልፀዋ፡፡

ምህረት በልቦናችን ቦታ የሚያገኘው ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ብቻ ስንታመን የእርሱን ፀጋ ሳንስለች ስንለምን እንደሆነ አያይዘው ገልፀዋል፡፡ ለዚሁም በቅርብ የምናውቃቸውና ዛሬ በሕይወት የሌሉ ለምህረት ሥራ ተምሳሌት የሆኑትን ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ገድል ተናግረዋል፡፡ በቅዱስነታቸው ላይ መልካምነት ለማሰብ ባልታደሉ ክፍሎች በተሴረው የግድያ ሙከራ አካላቸው በጥይጥ አረር እጅግ ቢጎዳም ከሞት ለመትረፍ ችለዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ግድያ በሞከረባቸው ወጣት ቂም ሳይዙ ይቅርታ እንዳደረጉለትና ከዚያም አልፎ በእስር ላይ እያለ እንደጠየቁት ዓለም የሚያውቀው የቅርብን ጊዜ ትውስታ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በሀገራችንም ተመሳሳይ ታሪኮች እንዳከሉ እናውቃለን ብለዉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረን  ፀሎት “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በልልን” ስንልና ይህን ስንፈጽም የምህረት መሳሪያ መሆን ካልቻልን የምንለምነው ሁሉ ፍሬ አያፈራም በማለት ለክርስትና ሕይወት ምህረት ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም “ዛሬ የቤተክርስቲያንን ልዩ የምህረት በር ስንዘጋ የእግዚአብሔር ምህረት ግን ዘላለማዊ በመሆኑ የልባችንን በር ለእርሱ መክፈታችን አንተው” በማለት ስብከተ ወንጌሉን አሰምተዋል፡፡

በቅዳሴው መጨረሻ ክብር አባ ጴጥርስ በርጋ የአዲስ አበባ ሰበካ ሐዋርዊ ሥራ የበላይ ሃለፊ በሰበካው ያታቀዱት “ከክርስቶስ ጋር በጋራ መጓዝ” በማለት በጋራ የጸደቀው የሰበካው ሰነድ  ጅማሬ መልካም እንደሆነ ገልጸዉ ይህንኑ የሰበካውን እቅድ በተጀመረው የአንድነት ጉዞ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ጠንክረን መስራት አለብን በማለት  አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪ  የክርስቶስ ንጉስ በዓል በብሔራው ደረጃ እንዲከበር አስተዋጽኦ ላደረጉት ሁሉ አመስግነዉ ይህ መንፈሳዊ እንድነት ተጠናክሮ መጓዝ  እንዳለበትና ያም የክርስቶስን ምስክርነት የበለጠ ለማሳደግ የበለጠ ይረዳል ብለዋል፡፡

በቅዳሴው መጨረሻ የልደተ ማርያም ካቴድራል ቁምስና የኢዮቬልዩ ዓመት በርን ብፁዕነታቸው በፀሎተ ብራኬ የዘጉ ሲሆን ምዕመኑ “በምህርቱ ባለ ጸጋ ነው፣ የኛ እግዚአብሔር ሁሌ ፍቅር ነው” እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና በማቅረብ ደስታቸውን በእልታና በዝማሬ ገልጸዋል፡፡

ከቅዳሴ መልስ በቅዱስ ቶማስ አኳይነስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ጊቢ በቁምስናዎችና በገዳማት የተዘጋጁ አውደ ርዕይና  የተለያዩ ጨዋታዎች ቀርበዋል፡፡

ቤተክርስቲያን ይህን ልዩ የምህረት ዓመት አዋጃ ጥሪ ስታቀርብ ሰዎች ሁሉ በመንፈሳዊ ሆነ በአካላዊ  የምህረት ሥራ ትጉህ በመሆን የክርስቶስ የምህረት ስራ ምሳሌ በመፈጸም መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድግ ለማድረግና ለመርዳት ነው፡፡ እንደአለፉት ዘመናት መጪውንም ጊዜ ክርስትናችንን የበለጠ ጠብቀን እንድናሳድግ ይረዳን ዘንድ በአንድ መንፈሳዊ ርዕስ ላይ ትኩረት በመስጠት ልጆችዋ በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲያድጉ የተቻላትን እያደረገች ትገናለች፡፡ ይህ በዓል በሁሉም ሀገረስብከት የተደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት እትማችን ይዘን እንቀርባለን፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *